አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከአሜሪካ ግምጃ ቤት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
ከዓለም ባንክ እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን በተደረገው ውይይት ሁለቱ ወገኖች በሀገራቱ የጋራ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በተለይም አሜሪካ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ እያደረገችው ያለውን ድጋፍና የሁለቱን ሀገራት የንግድና የኢንቨስትመንት ትብብር ማጠናከር የተመለከቱ ጉዳዮች በውይይቱ ላይ ተነስተዋል፡፡
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት፥ ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገችው በምትገኘው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ ለሥራ ኃላፊዎቹ ገለጻ አድርገዋል፡፡
መንግስት በተለይም የአስተዳደር ስርዓቱን ለማጠናከር እንዲሁም የሀገሪቱን የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢ ለማሻሻል ቁርጠኛ መሆኑንም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
የሥራ ኃላፊዎቹ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተገኙ ውጤቶችን አድንቀው፥ አሜሪካ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመተባበር እንዲሁም የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማሳደግ የኢኮኖሚ ሽግግሩን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች መሰል ውይይቶችን በማስቀጠል የጋራ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የኢኮኖሚ ዘርፎች ለማጠናከር እንዲሁም ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ይበልጥ ተቀራርበው ለመስራት ተስማምተዋል፡፡

