አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቀድሞ የፕራይቬታይዜሽን እና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ በመንግስት ላይ 52 ሚሊየን ብር ኪሳራ አድርሰዋል የተባሉ ሦስት ግለሰቦች በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
ተከሳሾቹ በመንግስት ይዞታ ስር ሲተዳደር የነበረው አደይ አበባ ድርና ማግ ፋብሪካ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ልብስ ስፌትና ጨርቃ ጨርቅ አ.ማ እንዲቀየር አድርገዋል በሚል ነው ክስ የተመሰረተባቸው።
1ኛ ተከሳሽ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር የነበሩት በየነ ገ/መስቀል ማዳ፣ 2ኛ ተከሳሽ የኤጀንሲው የድህረ ፕራይቬታይዜሽን ንግድና አገልግሎት ዘርፍ ዳይሬክተር ታዬ አድማሱ አዘነ እንዲሁም 3ኛ ተከሳሽ የቢኤም ኢትዮጵያ ልብስ ስፌትና ጨርቃ ጨርቅ አ.ማ ስራ አስኪያጅ የነበሩት ዋን ሚዩንግ ራዩ ናቸው፡፡
1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የማይገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በግል ሥራ ዘርፍ ከተሰማራው 3ኛ ተከሳሽ ጋር በጥቅም በመመሳጠር ፋብሪካውን ተገቢ ባልሆነ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ልብስ ስፌትና ጨርቃ ጨርቅ አ.ማ እንዲቀየር ማድረጋቸው በክሱ ላይ ተመልክቷል፡፡
አደይ አበባ ድርና ማግ ብሎክ-2 ፋብሪካ በጋራ ኢንቨስትመንት ስምምነት ከግል አልሚ ባለሀብቶች ጋር አክሲዮን ማህበር ሆኖ እንዲመሰረት በቦርድ በተወሰነው መሰረት በቀን 08/02/2003 ዓ.ም 1ኛ እና 3ኛ ተከሳሽ የጋራ ኢንቨስትመንት ስምምነት ውል መፈራረማቸውን የክስ መዝገቡ አስታውሷል፡፡
3ኛ ተከሳሽ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብር ምንዛሪ ተመን የሚሰላ 10 ሚሊየን 993ሺህ ዶላር በአክሲዮን ድርሻን መመዝገብ እንዳለበትና ከዚህ ውስጥ 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር በወቅቱ የምንዛሪ ስሌት 52 ሚሊየን 576 ሺህ ብር መክፈል እንዳለባቸው በስምምነቱ ተካቷል፡፡
ይህ ካልተፈጸመ አክሲዮን ማህበሩ እንደማይቋቋምና ውሉም እንዳልተፈጸመ እንደሚቆጠር ተዋውለው የነበረ ቢሆንም ስምምነቱን በሚጣረስ መልኩ 3ኛ ተከሳሽና እሱ የመረጣቸው ሌሎች ሦስት ባለድርሻዎች ያልተገባ ጥቅም እንዲያገኙ በማሰብ 1 ሚሊየን 643 ሺህ ብር ብቻ በመከፍል ፋብሪካው ቢኤም ኢትዮጲያ ልብስ ስፌትና ጨርቃ ጨርቅ አ.ማ ሆኖ እንዲመሰረት ማድረጋቸው በክስ ዝርዝሩ ላይ ሰፍሯል ፡፡
በዚህም ዐቃቤ ህግ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች መንግስት ከተከፈለ አክሲዮን ድርሻ መዋጮ ማግኘት ያለበትንና ሊጠብቁት የሚገባ 52 ሚሊየን 576 ሺህ ብር ጥቅም በማሳጣት እንዲሁም 3ኛ ተከሳሽ የማይገባ ጥቅም እንዲያገኝ አድርገዋል በማለት በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 (1) (ሀ)፣ 33 እና 411 (1) (ሀ) (ሐ) (2) ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ በዋና ወንጀል አድራጊነት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል፡፡
በተጨማሪም 3ኛ ተከሳሽ በልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት የመንግስት ሥራን በማይመች አኳኋን መምራት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ችሎት ተከሳሾቹ ቀርበው ክስ ከተነበበላቸው በኋላ የክስ መቃወሚያን ለመጠባበቅ ለጥቅምት 17/2018 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በሲፈን መኮንን