Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ዓለም አቀፍ ትብብሮችን ለማሳካት መሰረት የሚጥል ነው – ሰላማዊት ካሳ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ዓለም አቀፍ ትብብሮችን ለማሳካት መሰረት የሚጥል ነው አሉ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፡፡

የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) በጣልያን ሮም 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ሁነቶች ማክበሩ ይታወሳል፡፡

ሚኒስትሯ ጉዳዩን አስመልክተው ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ ÷ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለሌሎች ሥራዎች ግብዓት የምናገኝበት እና ዓለም አቀፍ ትብብሮችን ለማሳከት መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለዓለም ምሳሌ ይሆናሉ ተብለው ከተመረጡ ዋና ዋና ሥራዎች ውስጥ አንዱ ሆኖ መመረጡን አመልክተዋል፡፡

ያከናወንነው ሥራ ፍሬ አፍርቶ ያየንበት መድረክ ነው ያሉት ሚኒስትሯ ÷ ይህ ዕውቅና ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ኢትዮጵያዊያን በጋራ ቆመን ካሳካነቸው ሥራዎች ውስጥ አንዱ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

በመድረኩ የዲፕሎማሲ ስኬቶች ጭምር እንደነበሩ ጠቅሰው÷ኢትዮጵያ መስፈርቶችን አሟልታ የልማት አጀንዳዎቿን እየቀረፀች መሆኑ ሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ሊወስዱበት እንደሚገባ መነሳቱን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻል የምታደርገው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ መሆን እንደሚችል በመድረኩ መጠቀሱን አስታውሰዋል፡፡

በርካታ ሀገራት ከኢትዮጵያ ልምድ መውሰድ እንደሚፈልጉ ፍላጎታቸውን ያሳዩበት መድረክ ነበር ነው ያሉት፡፡

ከዚህ በኋላ ለሚሰሩ ማሕበረሰብ ተኮር ሥራዎች ብዙ ድጋፍ ማግኘት የሚያስችል ውይይት መደረጉንም አመልክተዋል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

Exit mobile version