አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ 2ኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ 2ኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የምስጋና መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት 2ኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ በስኬት እንዲጠናቀቅ በከፍተኛ የሥራ ተነሳሽነት ሌት እና ቀን ሲሰሩ ለነበሩ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ከንቲባዋ ከማዕከል እስከ ወረዳ ያሉ አመራሮችና ሰራተኞች፣ ኮንትራክተሮች፣ አማካሪዎች፣ ማህበራት፣ በጎ ፈቃደኞችና ሌሎችም አካላት ለነበራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦና ትውልድ ተሻጋሪ ሥራ ነው ያመሰገኑት፡፡
በተለይም መላው የመዲናዋ ነዋሪ ለሚነዙ ሀሰተኛ አሉባልታዎች ጆሮ ሳይሰጥ (የልማት ተነሺ የሆኑትም ያልሆኑትም) ለጋራ ልማት በመተባበር፣ ቡና እያፈላ፣ ውሃ እያቀረበ ለልማት ሥራው ውጤታማነት ላሳየው ከፍተኛ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በ2ኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ የተከናወኑ ሥራዎች አራት ሲሆኑ እነዚህም (1) ከመስቀል አደባባይ መገናኛ – ሳውዝ ጌት፣ (2) ከአንበሳ ጋራዥ -ጎሮ ፣ (3) ከአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬሽን ማዕከል ፣ ጎሮ ፣ ቦሌ ቪ አይ ፒ ተርሚናል (4) ከሳር ቤት – ጀርመን አደባባይ ፣ጋርመንት ፉሪ አደባባይ ናቸው፡፡
በ1ኛ እና 2ኛ ዙር የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከተጠናቀቁ መሰረተ ልማቶች መካከል 342 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ ፣ 185 ኪሎ ሜትር የተሽከርካሪ መንገድ ፣241 ኪሎ ሜትር የሳይክል መንገድ እና ዘመናዊ የመንገድ መብራቶች ይገኙበታል፡፡
በተጨማሪም በርካታ የሕዝብ መገልገያ እና መዝናኛ ቦታዎች ፣ በርካታ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶች፣ 101 የህፃናት መጫወቻዎች፣ 155 የስፓርት ማዘውተሪያዎች፣ 153 ዘመናዊ ፓርኪንግ እና ተርሚናሎች እንዲሁም 210 የሕዝብ መጸዳጃዎች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ተመላክቷል፡፡

