Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአፋር ክልል በጎርፍ ውሃ የተከበቡ ወገኖችን በሄሊኮፕተር የማውጣቱ ስራ መጠናቀቁ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 12 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአፋር ክልል በጎርፍ ተከበው የነበሩ ወገኖችን በሄሊኮፕተር ታግዞ የማውጣቱ ስራ መጠናቀቁን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የመከላከያ እና አየር ኃይል አባላት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የክልሉ መንግስትና ህዝብ ከፍተኛ ምስጋናና አክብሮት እንዳላቸውም ተገልጿል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን በክልሉ ዘንድሮ የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ በአዋሽ ዳር የሚገኙትን ጨምሮ በ11 ወረዳዎች ከ67 ሺህ ሰዎች በላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል።

ክእነዚህ ውስጥ ከ40 ሺ 700 በላይ ሰዎች በጎርፉ ምክንያት ከመኖሪያ አካባቢያቸው መፈናቀላቸውን ተናግረዋል።

ብዛት ያላቸው ሰዎችም በጎርፍ ውሃ ተከበው ለአደጋ ተጋልጠው እንደነበር አውስተዋል።

ክልሉ ከኢፌዲሪ መከላከያ እና አየር ኃይል ጋር በመተባበር ላለፉት አስር ቀናት በሄሊኮፕተሮች በመታገዝ በውሃ ተከበው የነበሩ ሰዎችን የማውጣትና አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የማድረሱ ስራ በትጋት ሲያከናውን ቆይቷል ብለዋል።

በዚህም በአሳኢታ፣ አፋምቦ እና ገረኒ ወረዳዎች በውሃ ተከበው የነበሩ 4 ሺ 915 ሰዎችን በሁለት ሄሊኮፕተሮች በመታገዝ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲወጡ በማድረግ ትናንት በስኬት ማጠናቀቅ መቻሉን አቶ መሐመድ አስታውቀዋል።

3 ሺህ 640 ሰዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ በደራሽ ጎርፍ ተከበው የነበሩባቸው አካባቢዎች መከላከያ እና አየር ኃይል አስቸኳይ ምግብና ምግብ ነክ ቁሳቁሶችን ድጋፍ በማድረግ የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በዚህም በክልሉ ተከስቶ በነበረው የጎርፍ ውሃ ምክንያት አንድም የሰው ህይወት እንዳይጠፋ በተለይ የምስራቅ ዕዝ አየር ኃይል አባላት የላቀ አስተዋጽኦ አድርገዋል ብለዋል።

የሰራዊቱ አባላት እራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ወገናቸውን ለመታደግ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የክልሉ መንግስትና ህዝብ ከፍተኛ ምስጋናና አክብሮት ያላቸው መሆኑን አቶ መሐመድ አስታውቀዋል።

Exit mobile version