አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግስት የነደፈውን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እውን ለማድረግ የተጠናከረ የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓትን በሁሉም የአስተዳደር መዋቅሮች መዘርጋት ይገባል አሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጀው ዓመታዊ የፋይናንስ ዕውቀት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ነው።
ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ መርሐ ግብሩ የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓትን ይበልጥ ለማሻሻል እየተደረገ ያለውን ጥረት ያግዛል ።
መንግስት የነደፈውን ኢኮኖሚያዊ ልማት እውን ለማድረግ የተጠናከረ የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓት በሁሉም የአስተዳደር መዋቅሮች መዘርጋት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የፋይናንስ አስተዳደር የመንግስትን ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች በማስፈጸም የተፈለገውን ስኬት ለማምጣት እንደሚረዳ አመልክተዋል፡፡
ጠንካራ የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓት ለመተግበር በሁሉም የአስተዳደር እርከን የሚገኙ አካላት ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይገባል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ም/ገዥ አማካሪ ማርታ ኃይለማርያም በበኩላቸው ÷ መድረኩ የፋይናንስ ተቋማት፣ የመንግስት አካላትና የልማት ድርጅቶችን በጋራ በማገናኘት የተቀናጀ የፋይናንስ እውቀት ለማስረጽ ያለመ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በረጅም ዕቅድ የያዘችውን ጠንካራ፣ ተደራሽ፣ ዘመናዊ እና ፍትሃዊ የፋይናንስ ሥርዓት ለመገንባት እንደሚያግዝም አመልክተዋል፡፡
በዳንኤል አማረ

