Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አዲስ ገቢ ተማሪዎችን መቀበል ጀምረዋል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በትምህርት ሚኒስቴር ምደባ መሰረት አዲስ ገቢ ተማሪዎችን መቀበል ጀምረዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር በ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ወስደው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመግቢያ ነጥብ ያመጡና በሪሚዲያል ፕሮግራም ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎችን ምደባ አከናውኗል።
በዚህም መሰረት ዩኒቨርስቲዎች ሚኒስቴሩ የመደበላቸውን ተማሪዎች መቀበል መጀመራቸውን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አለምሸት ተሾመ እንዳሉት፥ በዩኒቨርስቲው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ከ5 ሺህ 5ዐዐ በላይ ተማሪዎች ተመድበዋል።
በዚህም ዩኒቨርሲቲው ለመማር ማስተማር ሂደቱ አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ዝግጅቶችን በማድረግ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን መቀበል ጀምሯል ብለዋል።
በተመሳሳይ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ሚኒስቴር የተመደቡለትን ከ1ሺህ 700 በላይ አዲስ ተማሪዎችን እየተቀበለ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አገልግሎት ዲን ጊዜው ፈጠነ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲው በ2017 የሪሚዲያል ትምህርት ተከታትለው ያለፉ ከ600 በላይ ተማሪዎችን እየተቀበልን እንገኛለን ነው ያሉት።
ዩኒቨርሲቲው ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የወሰደውን የቃል ኪዳን ቤተሰብ ፕሮግራም “የሸዋ የቃል ኪዳን ቤተሰብ” በሚል በዚህ ዓመት መተግበር እንደሚጀምር አስረድተዋል።
በዚህም ተማሪዎችን ከቃል ኪዳን ቤተሰቦች ጋር የማረካከብ ስራ በቅርብ ቀናት ውስጥ ይጀመራል ነው ያሉት።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ ተንሳይ ኃይሉ በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው በመደበኛና የሪሚዲያል ፕሮግራም ትምህርታቸውን የሚከታተሉ 4 ሺህ 67 አዲስ ገቢ ተማሪዎችን መቀበሉን ጠቁመዋል፡፡
በተሾመ ኃይሉ እና አበበ የሸዋልዑል
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!
Exit mobile version