Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በ2 ሚሊየን ፓውንድ ዩናይትድን የተቀላቀለው ኤድዊን ቫንደርሳር…

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ማንቼስተር ዩናይትድ በክለቡ ታሪክ ከተመለከታቸው ምርጥ ግብ ጠባቂዎች መካከል አንዱ የሆነው ኤድዊን ቫንደርሳር ዩናይትድን የተቀላቀለው በ2 ሚሊየን ፓውንድ ብቻ ነበር፡፡

በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የተጫዋችነት ህይወቱን በሀገሩ ክለብ አያክስ የጀመረው ቫንደርሳር የክለቡ ወርቃማ ትውልድ አባል ነበር፡፡

በፈረንጆቹ 1995 የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ አሸናፊ የነበረው የኔዘርላንዱ ክለብ አያክስ አምስተርዳም ስብስብ አካል እንደነበር ይታወሳል፡፡

ቫንደርሳር ከምን ጊዜም ምርጥ ግብ ጠባቂዎች አንዱ ሲሆን፥ በእግር ኳስ ሕይወቱ 26 ዋና ዋና ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡

በማንቼስተር ዩናይትድ ቤት ቆይታው በዋንጫ የታጀቡ ዓመታትን ማሳለፍ የቻለው ግብ ጠባቂው የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግና የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን ጨምሮ የተለያዩ ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል፡፡

ቫንደርሳር በፈረንጆቹ 2008/09 የውድድር ዘመን ለተከታታይ 14 ጨዋታዎችን (1 ሺህ 311 ደቂቃዎችን) በሊጉ ጎል ሳይቆጠርበት መጓዝ የቻለ ድንቅ ግብ ጠባቂ እንደነበርም ይታወሳል፡፡

በፈረንጆቹ 2010/11 የውድድር ዓመት ከማንቼስተር ዩናይትድ ጋር በ40 ዓመት ከ205 ቀን እድሜው የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት የቻለ አንጋፋው ተጫዋች ነው።

በ1995 እና 2009 የአውሮፓ ምርጥ ግብ ጠባቂ እንዲሁም በ2009 የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የዓመቱ ምርጥ ስብስብ ውስጥ የተካተተው ቫንደርሳር እነዚህን ጨምሮ በርካታ የግል ሽልማቶችን አሸንፏል።

ከፈረንጆቹ 2005 እስከ 2011 ድረስ በማንቼስተር ዩናይትድ የተጫወተው ግብ ጠባቂው ከቀያይ ሰይጣኖቹ በተጨማሪ ለዩቬንቱስ፣ አያክስ እና ፉልሃም መጫወቱ አይዘነጋም፡፡

ከማንቼስተር ዩናይትድ ጋር የሊጉን ዋንጫ ደጋግሞ ያሳካው ቫንደርሰር በፈረንጆቹ 2010/11 የውድድር ዓመት መጨረሻ የሊጉን ዋንጫ ካሳካ በኋላ ከዩናይትድ ጋር ተለያይቷል፡፡

የኔዘርላንድ ብሔራዊ ቡድንን ከፈረንጆቹ 1995 እስከ 2008 ድረስ በግብ ጠባቂነት ያገለገለ ሲሆን፥ ዓለም ዋንጫን ጨምሮ በተለያዩ ውድድሮች 130 ጨዋታዎችን ማድረግ ችሏል፡፡

ግብ ጠባቂውን በ2 ሚሊየን ፓውንድ የዝውውር ሂሳብ ለማንቼስተር ዩናይትድ ያስፈረሙት የወቅቱ የክለቡ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ከፒተር ሽማይክል በኋላ ለዩናይትድ የተጫወተ ምርጥ ግብ ጠባቂ በማለት ያሞካሹታል፡፡

በፈረንጆቹ 2008/09 የውድድር ዘመን የፕሪሚየር ሊጉን የወርቅ ጓንት ማሸነፍ ችሏል፡፡

እንዲሁም በዚሁ የውድድር ዓመት የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ዩናይትድ ሲያሳካ የመጨረሻውን የፍፁም ቅጣት ምት በማዳን ትልቁን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡

ከምንጊዜም ምርጥ ግብ ጠባቂዎች መካከል አንዱ የሆነው የቀድሞ የማንቼስተር ዩናይትድ ግብ ጠባቂ ኤድዊን ቫንደርሳር በፈረንጆቹ 1970 በዛሬዋ ዕለት ነበር የተወለደው፡፡

በወንድማገኝ ፀጋዬ

Exit mobile version