Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በቆመ ኳስ አጠቃቀሙ እየተሞካሸ የሚገኘው ጋብርኤል ማጋሌሽ…

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቆመ ኳስ አጠቃቀሙ እየተሞካሸ የሚገኘው የአርሰናል የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ጋብርኤል ማጋሌሽ።
አርሰናል በክፍት ጨዋታ ግብ ማስቆጠር ሲሳነው የመጨረሻ ካርዱ በማድረግ የሚመዘው ተጫዋች ሆኗል ጋብርኤል ማጋሌሽ፡፡
የተወለደው በፈረንጆቹ 1997 በብራዚል ሳኦፖሎ ሲሆን÷ የእግር ኳስ ሕይወቱን የጀመረው በሀገሩ ክለብ አቫይ ነው።
በ2016 ለፈረንሳዩ ክለብ ሊል ዝውውሩን ያደረገው ማጋሌሽ÷ ወደ ክለቡ ሊል በ2018 ዳግም እስኪመለስ ለፈረንሳዩ ትሮይስ እና ለክሮሽያው ዳይናሞ ዛግሬቭ በውሰት ተጫውቶ አሳልፏል።
በ2020 ለሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል በ27 ሚሊየን ፓውንድ ፊርማውን ያኖረው ተጫዋቹ÷ በአሁን ሰዓት እየተጫወቱ ከሚገኙ ምርጥ የመሃል ተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሆኗል።
ማጋሌሽ በፈረንጆቹ 2023 ብራዚል ከቦሊቪያና ፔሩ ጋር ለነበራት የ2026 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ የወቅቱ ጊዜያዊ አሰልጣኝ በነበሩት አሰልጣኝ ፈርናንዶ ዲኒዝ የመጀመሪያ የብሔራዊ ቡድን ጥሪ ደርሶታል።
ከዚያ ጊዜ በኋላ ለብሔራዊ ቡድኑ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አንድ ግብ አስቆጥሯል።
ኃይል በተቀላቀለበት አጨዋወት፣ ከፍተኛ በሆነ አካላዊ ጥንካሬ እና በአየር ላይ ኳሶች ባለው ብልጫ የሚታወቀው ጋብርኤል ማጋሌሽ÷ ከእግር ኳስ ቤተሰቡ ከፍተኛ አድናቆት እየጎረፈለት ይገኛል፡፡
ማጋሌሽ በአሁን ሰዓት በራሱ እና በተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል ውስጥ የሚወስደው የበላይነት በብዙዎች እያስወደሰው ነው።
ማጋሌሽ ከቡድን አጋሩ ዊሊያም ሳሊባ ጋር የፈጠሩት ጥምረት ተቃራኒ ቡድኖች አርሰናል ላይ ግብ ማስቆጠር ከባድ እንዲሆንባቸው አድርገዋል።
ማጋሌሽ ከመከላከል ሚናው በተጨማሪ አርሰናል በክፍት ጨዋታ ግብ ማስቆጠር በሚቸገርበት ወቅት የቆሙ ኳሶችን በማስቆጠር የአጥቂ ሚናን የሚወጣ የወቅቱ ምርጥ ተከላካይ እንዲሁም በሰዓት አጠባበቁና በቦታ አያያዙ የሚደነቅ ለክለቡ የጭንቁ ሰዓት ደራሽ ተጫዋች እስከመሆን ደርሷል።
አርሰናል በ2025/26 የውድድር ዘመን እስካሁን ካደረጋቸው 9 የሊጉ ጨዋታዎች 22 ነጥቦችን በመሰብሰብ የሻምፒዮንነት ተስፋውን በማለምለም ቀጥሏል፡፡
ጥረት እና ትጋት ብሎም ወጥነት አሁን ላለበት ደረጃ ያደረሱት ጋብርኤል ማጋሌሽ÷ በታሪክ ምርጡ የሁለቱ ሳጥን ወራሪ በሚል ሲታወስ የሚኖርበትን ስራ በላቀ ደረጃ እየሰራ ይገኛል፡፡
በአቤል ነዋይ
Exit mobile version