Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአስደናቂ ውጤት የተጠናቀቀው የፕሬዚዳንት ትራምፕና ሺ ጂንፒንግ ውይይት…

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የቻይና አቻቸው ሺ ጂንፒንግ በደቡብ ኮሪያ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ በትኩረት መክረዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ÷ ከቻይና አቻቸው ሺ ጂንፒንግ ጋር ያደረጉት ውይይት አስደናቂ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

በሁሉም ጉዳዮች በሚባል ደረጃ ስምምነት ላይ መደረሱን ጠቁመው ÷ ይህም የሁለቱን ሃያላን ሀገራት ሁለንተናዊ ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡

በስምምነቱ መሰረት አሜሪካ በቻይና ሸቀጦች ላይ ጥላው የነበረውን ቀረጥ ከ57 በመቶ ወደ 47 በመቶ እንደምትቀንስ ነው ያስረዱት፡፡

ሀገራቱ በቅርቡ የንግድ ስምምነት የሚፈራረሙ ሲሆን ÷ ስምምነቱም ሁለቱ ወገኖች በኢኮኖሚ ዘርፍ የገቡበትን ውጥረት እንደሚያረግብው ይጠበቃል፡፡

ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ በበኩላቸው ÷ ቻይና እና አሜሪካ በተለያዩ ዘርፎች በትብብር በመስራት አጋርነታቸውንና ወንድማማችነታቸውን ይበልጥ ማጠናከር አለባቸው ብለዋል፡፡

ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገራቱ ለዓለም ኢኮኖሚ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት መወጣት አለባቸው ፤ ለዚህም ቀና ትብብርና የጋራ ተጠቃሚነት ወሳኝ ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በውይይቱ ከሞላ ጎደል በሁሉም ጉዳዮች ስምምነት ላይ መደረሱን ጠቁመው÷ ስምምነቱን ለመተግበርና የኢኮኖሚ መረጋጋት ለመፍጠር በትብብርና በቁርጠኝነት ይሰራል ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል ሀገራቱ በሳይበር ጥቃት፣ በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ በሕገ ወጥ ስደተኞች አያያዝ እና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፎች በትብብር ለመስራት ተስፋ ሰጪ ምክክር ማድረጋቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእስያ የነበራቸውን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ያጠናቀቁ ሲሆን ÷ በቀጣዩ ሚያዝያ ወርም በቻይና የሥራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተመላክቷል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version