አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፀሐይ መሸ ደህና እደሩ ብላ ቦታውን ለጽልመት ትታ ሄዳለች፤ ከአድማሱ ስር ደግሞ ከአንዲት ድክም ካለች ጎጆ ውስጥ የሚወጣው ጭስ ይትጎለጎላል። በዚህች ትንሽዬ ደሳሳ ጎጆ ውስጥ በሦስት ጉልቻ ላይ ተጥዳ የምትንተከተከውን ሽሮ እናት ዓይኖቿን ከጭሱ ለመሸሸግ እየሞከሩ ያማስሉታል።
አለፍ ብሎ ደግሞ ከመደብ ላይ የተቀመጡት አባት ወደ ጆሯቸው አስጠግተው የያዟትን ሬዲዮ ጥራት ለማስተካከል በኩራዝ ብርሃን ታግዘው በጣታቸው ይቃኛሉ፤ በኢንጂነሪንግ ሙያ የተመረቀች ልጃቸው ዓለም ደግሞ ከወደ ጥግ ተቀምጣ ልብሶችን ታስተካክላለች።
በዚህ መሃል ከወደ ሬዲዮዋ አንዳች የምስራች ተስተጋባ። ይህም የሕዳሴ ግድብ መሰረተ ድንጋይ የመቀመጥ ብስራት ነበር።
ይህንን የሰሙት አባት በቦታው ድረስ ሄደው ለዚህ ታሪካዊ ግንባታ የበኩላቸውን ለማድረግ የዕድሜ ነገር እንደሚገድባቸው አስበው ትካዜ ገባቸው። ልጃቸው ዓለም ግን በዚህ ታላቅ ታሪካዊ ስራ ላይ የበኩሏን ለማበርከት በቀዬዋ ተቀምጣ መኳል እና ማግባት ትታ ወደ ጉባ አቀናች።
የልጃቸው መነሳት የተመለከቱት ቤተሰብም በድል ወደ ቤቷ እንድትመለስ አደራ ብለው መርቀው ይልኳታል።
መጠናቀቂያው ከተጠበቀው ጊዜ በላይ በረዘመው የግድቡ ግንባታ ላይ ሃሩሩን እና ቁሩን በመጋፈጥ የአባቷን አደራ በልቧ ሰንቃ ከተራራው እና ሸንተረሩ ጋር ትግል ገጠመች።
ህልውናን በሚፈትኑ ውጣ ውረዶች እና የቤተሰብ ናፍቆት ውስጥ የጉባ በረሃ ውስጥ ውስጧን ቢያዳክማትም በሀገር ፍቅር እና በጀግንነት ስሜት ለማሸነፍ መታገሏን አላቋረጠችም።
በዚህ ሁሉ ውጣውረድ ከቤተሰቦቿ ጋር ለመገናኘት እንኳን ጊዜ አላገኘችም። የሰፈር ጓደኞቿ ሲያገቡ እሷ ከሃሩር ጋር ትተናነቅ ነበር፤ አብሮ አደግ ጓደኞቿ ልጅ ሲወልዱ እሷ ከወንዝ ጋር ትፋለም ከሞገድ ጋር ትዋደቅ ነበር።
በመጨረሻም ያቺ ደሳሳ ቤት ተጠናክራ ቆማለች፤ በውስጧ በበራው አምፖል ቤቱ በብርሃን ተሞልቷል፤ ሬዲዮኑም እንደ ወትሮው መንኮሻኮሹን ትቶ ጥርት ያለ ድምጽ ያስተላልፋል።
ከሬዲዮ ጎን የተቀመጠው አባት ከዓመታት በኋላ ሌላ አዲስ የብስራት ዜና ከዚሁ ሪዲዮ ደረሳቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት በስኬት በመጠናቀቁ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክትም አስተላለፉ።
ከዓመታት በፊት የተጀመረ የሀገር ኩራትና የታሪክ ዐሻራ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዕውን እንዲሆን ልጃቸው ዓለም ጉልበቷን ሳትሰስት፣ ዕድሜዋን ሳትቆጥብ፣ ዕውቀቷን በመጨረሻም ሕይወቷን በመስጠት ፕሮጀክቱ ዕውን እንዲሆን የበኩሏን አድርጋለች።
ይህንን ከላይ የተገለጸውን ታሪክ በአጭር ፊልም የሰራችው ቲክቶከር ሔርሜላ መድፉ ወይም በቲክቶክ ስሟ ባዚ የታሪኩ ዓላማ በሕዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ሰራተኞችን ለማሰብ እንደሆነ ትናገራለች።
ግድቡ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ ሁሉ ነገራቸውን ትተው በትጋት በመስራት ግድቡ ዕውን እንዲሆን አስተዋጽዖ ያበረከቱ ሰራተኞች ሊመሰገኑ ይገባል የምትለው ሔርሜላ÷ “ያልተዘመረላቸው ጀግኖች” በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን ይህንን አጭር ፊልም ከባልደረቦቿ ጋር ማዘጋጀታቸውን አንስታለች።
በአጭር ፊልሙ ላይ ዋና ገጸ ባህርይ የሆነችው ዓለም አብዛኛውን ሰራተኞች የምትወክል እንደሆነች እና ሰራተኞቹ ያላቸውን ቁርጠኝነት እና የሀገር ፍቅር ስሜት የምታንጸባርቅ መሆኗን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግራለች።
የኛ ዘመን ኢትዮጵያውያን በአንድነት ተባብረው የገነቡት እና የሀገር ኩራት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጀምሮ የተጠናቀቀበት መሆኑ እንደ ጀብድ የምናነሳው ጉዳይ ነው የምትለው ሔርሜላ÷ በቦታው ላይ በመገኘት ቀረጻ ባደረጉበት ወቅት አካባቢው ከአየር ጸባዩ በጣም አስቸጋሪ እንደነበር አስታውሳለች።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተገንብቶ መጠናቀቁ ማሳካት እንደምንችል ምሳሌ እንደሆነ በመግለጽ÷ በቀጣይም እንደ ሕዳሴ ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በአንድነትና በጋራ ጥረት እንሰራለን በማለት ያላትን እምነት ገልጻለች።
በዮናስ ጌትነት
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

