አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዛሬ ምሽት በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ 4ኛ ዙር መርሐ ግብር ሊቨርፑል ከሪያል ማድሪድ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
በዚህ ጨዋታ የቀድሞ የሊቨርፑል ተጫዋች ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ የልጅነት ክለቡን በተቃራኒ የሚገጥም ይሆናል፡፡
እንግሊዛዊው የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች አርኖልድ በክረምቱ የተጫዋች ዝውውር መስኮት የስፔኑን ክለብ ሪያል ማድሪድን መቀላቀሉ ይታወሳል፡፡
አርኖልድ በሊቨርፑል በነበረው ቆይታ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ እና የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን ጨምሮ የተለያዩ ዋንጫዎችን አሳክቷል።
በሊቨርፑል ደማቅ የእግር ኳስ ሕይወት አሳልፎ ወደ ሪያል ማድሪድ ባደረገው ዝውውር የክለቡ ደጋፊዎች ደስተኞች አልነበሩም።
ዝውውሩ ተጠናቅቆ ሪያል ማድሪድን ሲቀላቀል የሊቨርፑል ደጋፊዎች አርኖልድ ክህደት ፈፅሞብናል በማለት ተቃውሞ ማሰማታቸው ይታወሳል፡፡
አርኖልድ ሪያል ማድሪድን ከተቀላቀለ በኋላ በቂ የመሰለፍ ዕድል ካለማግኘት በተጨማሪ በጉዳት ምክንያት ከሜዳ እየራቀ ይገኛል፡፡
ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ሜዳ የተመለሰው አርኖልድ ዛሬ የልጅነት ክለብ የሆነውን ሊቨርፑል በአንፊልድ ሮድ በተቃራኒ ሆኖ ይገጥማል፡፡
አርኖልድ ዛሬ ሊቨርፑልን የሚገጥመው የሪያል ማድሪድ ስብስብ ውስጥ የተካተተ ሲሆን÷ ጨዋታውን በቋሚነት ላይጀምር እንደሚችል እየተዘገበ ይገኛል።
አሌክሳንደር አርኖልድ ከጨዋታው ቀድሞ በሰጠው አስተያየት ሊቨርፑል ላይ ጎል ካስቆጠርኩ ደስታዬን አልገልፅም ሲል ተደምጧል።
ሪያል ማድሪድ እና ሊቨርፑል በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ መድረክ የፍጻሜ ጨዋታውን ጨምሮ በተለያዩ አጋጣሚዎች እርስ በርስ መገናኘታቸው ይታወሳል።
ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ባደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ሪያል ማድሪድ ሦስቱን ሲያሸንፍ÷ ሊቨርፑል በአንዱ ድል አድርጎ በአንዱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
ሪያል ማድሪድ በዚህ የውድድር ዘመን በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ያደረጋቸውን ሦስቱን ጨዋታ ማሸነፍ ችሏል።
በአሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ የሚመራው ሪያል ማድሪድ በስፔን ላሊጋም ሆነ በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ጥሩ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል።
ባለ ሜዳው ሊቨርፑል በበኩሉ÷ በሻምፒየንስ ሊጉ ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በአንዱ ሽንፈትን አስተናግዷል።
በአሰልጣኝ አርኔ ስሎት የሚመሩት ሊቨርፑሎች በውድድር ዘመኑ በሁሉም ጨዋታዎች ፈታኝ ጊዜን እያሳለፉ ይገኛል።
ሊቨርፑል ከሪያል ማድሪድ የሚያደርጉትን የሻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ሮማንያዊው ዳኛ ስቴቫን ኮቫክስ በመሐል ዳኝነት የሚመሩት ይሆናል።
ዋና ዳኛው በፈረንጆቹ 2022/23 የውድድር ዘመን ሪያል ማድሪድ ሊቨርፑልን በአንፊልድ 5 ለ 2 በሆነ ውጤት ያሸነፈበትን ጨዋታ መርተዋል።
ይህ ተጠባቂ ጨዋታ ዛሬ ምሽት 5 ሰዓት ላይ በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም ይደረጋል።
በወንድማገኝ ፀጋዬ

