አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ 4ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ምሽት ፒኤስጂ ከባየርን ሙኒክ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በተያዘው የውድድር ዓመት በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ያደረጓቸውን ሁሉንም ጨዋታዎች አሸንፈዋል፡፡
በዚህም ፒኤስጂ ተጋጣሚዎቹ ላይ 13 ግቦችን ሲያስቆጥር÷ ባየርን ሙኒክ ደግሞ 12 ግቦችን በተጋጣሚዎቹ መረብ ላይ አሳርፏል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም እርስ በርስ ባደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ባየርን ሙኒክ አራቱን ሲያሸንፍ ፒኤስጂ በአንዱ ድል አድርጓል፡፡
ፒኤስጂ በዚህ የውድድር ዓመት በሁሉም ውድድሮች ካደረጋቸው 14 ጨዋታዎች 10ሩን ያሸነፈ ሲሆን÷ በሶስቱ አቻ ተለያይቶ በአንዱ ሽንፈት አስተናግዷል፡፡
ባየርን ሙኒክ በበኩሉ በውድድር ዘመኑ በሁሉም ውድድሮች ያደረጋቸውን 15 ጨዋታዎች በሙሉ በማሸነፍ ተጋጣሚዎቹ ላይ 54 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡
የሁለቱ ቡድኖች ተጠባቂ ጨዋታ ምሽት 5 ሰዓት ላይ በፓርክ ደ ፕሪንስ የሚካሄድ ሲሆን ÷በተመሳሳይ ምሽት 5 ሰዓት ላይ ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ሮድ ሪያል ማድሪድን ያስተናግዳል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ባደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ሪያል ማድሪድ ሶስቱን ሲያሸንፍ ሊቨርፑል በአንዱ ድል አድርጎ በአንዱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
ሪያል ማድሪድ በዚህ የውድድር ዘመን በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ያደረጋቸውን ሶስቱንም ጨዋታዎች ማሸነፍ ችሏል።
ባለ ሜዳው ሊቨርፑል በበኩሉ በሻምፒየንስ ሊጉ ካደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በአንዱ ሽንፈት አስተናግዷል።
አትሌቲኮ ማድሪድ ከኡኒየን ሴንት ጊሎስ፣ ጁቬንቱስ ከስፖርቲንግ ሊዝበን፣ ኦሎምፒያኮስ ከፒኤስቪ፣ ቦዶ ግሊምት ከሞናኮ ሌሎች ምሽት 5 ሰዓት ላይ የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው፡፡
ከእነዚህ ጨዋታዎች አስቀድሞ ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ላይ ስላቪያ ፕራግ ከአርሰናል እንዲሁም ናፖሊ ከአይንትራክ ፍራንክፈርት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ

