Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማር የማምረት አቅም ጨምሯል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተተገበረ የሚገኘው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የማር ምርት እንዲጨምር አስተዋጽኦ አድርጓል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ብርሃኑ ኢትቻ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር መተግበር ከጀመረበት 2015 ዓ.ም ጀምሮ በተሰሩ ስራዎች አበረታች ውጤት ተገኝቷል።
‌‎
‎በመርሐ ግብሩ በወተት ላሞች፣ በእንስሳት ማድለብ፣ በዶሮ እርባታ፣ በዓሣ ልማት እንዲሁም በንብ ማነብ ሥራዎች ምርታማነትን በማሳደግ እና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ በኩል አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ የንብ ማነብ እንቅስቃሴ 109 የንብ መንደሮችን ለመመስረት የተያዘውን ግብ ለማሳካት የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ጠቅሰው፤ እስካሁን ድረስ 89 የማር መንደር ተመስርቷል ብለዋል።
ቀሪዎቹ የማር መንደሮች በተያዘው በጀት ዓመት እንደሚመሰረቱም አረጋግጠዋል።
በክልሉ 426 ሺህ 132 ባህላዊ የንብ ቀፎዎች መኖራቸውን የገለጹት ብርሃኑ ኢትቻ (ዶ/ር)፤ ዘመናዊ የንብ ቀፎ ቁጥርን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
11 ሺህ 560 ዘመናዊ እና 8 ሺህ 560 የሽግግር የንብ ቀፎ በክልሉ ይገኛል ነው ያሉት።
ዘመናዊ የንብ ቀፎ ከፍ ያለ ምርት የሚሰጥ በመሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ተጠቃሚ ለማድረግ
እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ወጣቶች በንብ ማነብ ሰፊ የስራ ዕድል እየተፈጠረላቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት የተተገበረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለንብ ማነብ ተግባር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ተናግረዋል።
በ2017 በጀት ዓመት በክልሉ 4 ሺህ 236 ቶን ማር መመረቱን አስታውሰው፤ ዘንድሮ የተሻለ ውጤት ይጠበቃል ብለዋል።
በአቢይ ጌታሁን
Exit mobile version