Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአማራ ክልል የደረሰ የጤፍ ሰብል ያለ ብክነት እንዲሰበሰብ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የምርት ብክነትን በሚቀንስ መንገድ የደረሰ የጤፍ ሰብልን ለመሰብሰብ እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ፡፡

በቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በመኸር እርሻ 900 ሺህ ሔክታር መሬት በጤፍ ሰብል ተሸፍኗል፡፡

አሁን ላይ የጤፍ ምርት እንደየአካባቢው ሁኔታ መሰብሰብ መጀመሩን ጠቁመው÷ ምርቱ ከብክነት በጸዳ መልኩ እንዲሰበሰብ አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

አርሶ አደሩ የደረሰን የጤፍ ምርት የርጥበት መጠኑን በጠበቀ ሁኔታ በጥንቃቄ መሰብሰብ እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት፡፡

በተለይም ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ምርቱ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ከስብሰባ በኋላም ሰብሉ በሚከመርበት ወቅት የእንጨት ርብራብ በመስራት ከመሬት ከፍ ብሎ መቀመጥ እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

ሰብሉን በፍጥነት መውቃት እንደሚገባ ያስረዱት ማንደፍሮ አስላከ (ዶ/ር)÷ በውቂያ ጊዜም የምርት ጥራትና ብክነት እንዳይከሰት ከስር ፕላስቲክ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የግብርና ባለሙያዎች ጤፍ በብዛት በሚመረትባቸው አካባቢዎች ለአርሶ አደሩ የግንዛቤ ማስጨበጥና ክትትል ሥራ እያከናወኑ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version