Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

“እናቴን ያሸነፋትን አሸንፌዋለሁ”

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጥቅምት በመላው ዓለም የጡት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ ወር ነው።

በኢትዮጵያ በዚህ ወር ስለካንሰር ተገቢው ግንዛቤ ይፈጠር ዘንድ የተለያዩ ሁነቶች ይዘጋጃሉ።

በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ነርስ ሲስተር ዓረፋይኔ ሰለሞን ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ የጡት ካንሰር ብዙዎችን እየፈተነ የሚገኝ ህመም ነው።

በበሽታው ከእሳቸው ባለፈ የቅርብ ወዳጅ ዘመዶች እንዲሁም ለህክምና የሚመጡ በርካታ ህሙማን ላይ አስከፊ ጉዳት ማስከተሉን በቅርብ መመልከታቸውን ተናግረዋል።

የህመሙን አስከፊነት መገንዘብ እንደሚገባ በመግለጽ፤ የቅድመ ክትትል ተግባር ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ሁሉም ሰው በተለይ ሴቶች በየጊዜው የጡት መጠንን በቤት ውስጥ መከታተል እና በተቻለ መጠን በየጊዜው ሀኪም ማማከር ይገባል ብለዋል።

ስንታመም በዙሪያችን ያሉ ሁሉ የእኛን ህመም ይታመማሉ በተለይ ለምንወዳቸው እንዳንጎድልባቸው አስቀድመን ራሳችንን መጠበቅ አለብን ነው ያሉት።

የምወዳትን እናቴን ስለነጠቀኝ የጡት ካንሰር ሰዎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የምችለውን ያህል እየሰራሁ ነው የሚሉት ሲስተር ዓረፋይኔ፤ የጡት ካንሰር በሰዓቱ ከታከምነው መዳን የሚችል ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ሴቶች የጡታቸውን መጠን ወይም ከጫፉ የመሰርጎድ አዝማሚያ ከተመለከቱ በአፋጣኝ ወደ ህክምና መሄድ እንዳለባቸውም ጠቁማለች፡፡

በካንሰር ምክንያት እናታቸውን ያጡት የጤና ባለሙያዋ፤ እሳቸውም በምርመራ የጡት ካንሰር ምልክት ሲታይባቸው ሁኔታውን ለመቀበል ተቸግረው እንደነበረ ያስታውሳሉ።

ነገር ግን ችግሩን በወቅቱ ማወቃቸው በህክምና ድነው አሁን ላይ በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙና በየጊዜው ክትትል እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የጡት ካንሰር በዘር ካለ የመያዝ እድላችን ከሌሎች በ50 በመቶ ይጨምራል በማለት ገልጸው፤ ከዛ ባሻገር ሰዎች ከመታመማቸው በፊት መከላከል ላይ እንዲያተኩሩ መክረዋል።

“እናቴን ያሸነፋትን አሸንፌዋለሁ” የሚሉት ሲስተር ዓረፋይኔ፤ ሰዎች በየወቅቱ ተገቢውን ክትትል ማድረግ እና ችግሩ ከተከሰተም በጊዜ ህክምና በማድረግ ጤናቸውን ለመመለስ ስለካንሰር ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ አለባቸው ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር የተወሰነ ሰዓት በእግር መንቀሳቀስ፣ ሁለት ሊትር ውሃ በየቀኑ መጠጣት የታሸጉና የተጠበሱ ምግቦችን ባለመመገብ ጤናቸውን እንዲጠብቁና ቢያንስ በዓመት አንዴ ወደ ህክምና ተቋማት በመሄድ ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በእየሩስ ወርቁ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

Exit mobile version