አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ገና በለጋ እድሜው ከቤት ወደ ትምህርት ቤት ደግሞም ከትምህርት መልስ ወደ ቤት ሦስት ኪሎ ሜትሮችን እለት እለት እየሮጠ ነው ያደገው፡፡
ትምህርትን አብዝቶ ይወድ ነበርና በጊዜው በትምህርት ፍቅሩ የተነሳ የሰርክ ተግባሩ የነበረው ሩጫ የማታ ማታ የስኬት ማማ መወጣጫ ሆኖታል።
በልጅነቱ አባቱን በሞት ማጣቱን ተከትሎ እሱንና ሌሎች እህትና ወንድሞቹን በብቸኝነት ካሳደገችው እናቱም አልፎ የትውልድ መንደሩን በብዙ የሚደግፍ ጀግና አትሌት ለመሆን በቅቷል።
የ41 ዓመቱ አትሌት ኤሊዩድ ኪፕቾጌ “በወቅቱ በየዕለቱ መሮጤን የግድ ትምህርት ቤት መሄድ ስላለብኝ እንጂ ከሯጭነት አንጻር አስቤው አላውቅም” ይላል፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኬንያ ናንዲ ግዛት ካፕሲስዋ በጀመረው የሩጫ መንገድ የዘመኑ ቀዳሚ የማራቶን ሯጭ እስከመሆን ዘልቋል። ኪፕቾጌ የ16 ዓመት ታዳጊ ሳለ ነበር ከቀድሞው ኬንያዊ አትሌትና ከወቅቱ አሰልጣኙ ፓትሪክ ሳንግ ጋር የተገናኘው።
የመጀመሪያው ስኬት የተጀመረውም በፈረንጆቹ 2003 በፈረንሳይ ፓሪስ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ነበር፡፡ በውድድሩ በ18 ዓመቱ በ5ሺህ ሜትር በቀዳሚነት በማጠናቀቅ የወርቅ ሜዳልያውን የግሉ አድርጓል።
በቀጣዩ ዓመት በአቴንስ ኦሎምፒክ በዚሁ ርቀት 3ኛ በመውጣት የነሀስ ሜዳልያ እንዲሁም በቤጂንግ ኦሊምፒክ 2ኛ በመሆን የብር ሜዳልያ አግኝቷል። ኪፕቾጌ በተለየ ሁኔታ በዓለም ላይ ስመጥር አትሌት ለመሆን የበቃው ግን በማራቶን ውድድሮች ነው፡፡
በተለይም ከፈረንጆቹ 2010 ጥቂት ዓመታት በፊትና በኋላ በ5ሺህ እና በ10ሺህ ሜትር የመም ውድድሮች ቀዳሚ ለመሆን በወቅቱ በአስደናቂ ብቃት ላይ ከነበሩት ቀነኒሳ በቀለ እና ሞ ፋራህ ጋር መፎካከር ግድ የሆነበት ኪፕቾጌ ትኩረቱን ወደ ማራቶን አደረገ፡፡
የተሻለ ውጤታማ እሆንበታለሁ ብሎ ያሰበውን የጎዳና ውድድር በግማሽ ማራቶን ከሞከረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀምቡርግ ማራቶን በመካፈል 2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ30 ሰከንድ በመግባት በበላይነት አጠናቀቀ፡፡
ወደ ማራቶን ጠቅልሎ በመግባት ከጥቂት ወራት በኋላ በዚያው በጀርመን በበርሊን ማራቶን ተሳትፎ 2ኛ በመሆን ማጠናቀቅ ችሎ ነበር፡፡
ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት በኦስትሪያ ቪዬና በተደረገ ውድድር ላይ 1 ሰዓት ከ59 ደቂቃ ከ40 ሰከንድ በመግባት ብቸኛው አትሌት ለመሆን በቅቷል፡፡
በርግጥ ኪፕቾጌ ከ2 ሰዓት በታች በመግባት ብቸኛ የሆነበት ማራቶን ለሁሉም አትሌቶች ክፍት ያልነበረና አሯሯጮች ተመድበውለት የተደረገ ሩጫ ሲሆን፥ በይፋ የዓለም ክብረወሰን ሆኖ አልተመዘገበም።
ከፈረንጆቹ 2014 እስከ 2019 በዋና ዋና የማራቶን ውድድሮች ያለማንም ተቀናቃኝ በብቸኝነት ማሸነፍ የቻለ ሲሆን በሪዮ እና ቶክዮ ኦሎምፒክ በማራቶን የወርቅ ሜዳልያን አግኝቷል፡፡
የበርሊን ማራቶንን አምስት ጊዜ በማሸነፍ ብቸኛው አትሌት ሲሆን የለንደን ማራቶንን አራት ጊዜ ማሸነፍ ችሏል፡፡ ኪፕቾጌ ኦሎምፒክን ጨምሮ በዋና ዋና የማራቶን ውድድሮች 13 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚው አትሌት ነው፡፡
በኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር ሁለት የወርቅ ሜዳልያ በማግኘት ከአትሌት አበበ ቢቂላ እና ዋልድማር ቼርፒንስኪ ጋር ታሪክ ይጋራል፡፡
ማራቶን ለሁለት ሰዓት ያህል የሚደረግ ሩጫ እንደመሆኑ ከፍ ያለ ዝግጅት እንደሚጠይቅ የሚገልጸው ኪፕቾጌ፥ ይህ ፈታኝ ልምምድ ለጥረቴ ዋጋ እንድሰጥ እንዲሁም ጥንካሬና ወጥ ብቃት እንዲኖረኝ ረድቶኛል ይላል፡፡
የማራቶን ውድድርን ገና በልምምድ ወቅት ማሸነፍ አለብኝ የሚል እምነት ስላለኝ የማደርገው ዝግጅት ህመም ያለው ቢሆንም ዓላማዬን ስለማሳካበት እደሰታለሁ ሲል ተናግሯል፡፡
የረዥም ርቀት ሩጫ ከእግር ይልቅ የአዕምሮና የልብ ውድድር እንደሆነም ነው የሚገልጸው፡፡
ከቀናት በፊት በኒውዮርክ ማራቶን የተሳተፈ ሲሆን፥ ይህ ውድድር በትልቅ ደረጃ ከሚጠቀሱ የማራቶን ውድድሮች የመጨረሻው ተሳትፎው ሊሆን እንደሚችል ገልጿል፡፡
ለብዙዎች የመቻል፣ የወጥ ብቃትና የጥንካሬ ምሳሌ ተደርጎ የሚነሳው ኤሊዩድ ኪፕቾጌ በሁሉም አህጉራት በመሮጥ ህልሙን እውን ለማድረግና ሰዎችን ለስፖርት ለማነሳሳት በማለም በቀጣይ በአንታርክቲካ እንደሚሮጥ ተናግሯል፡፡
ኪፕቾጌ በስፖርቱ ዘርፍ በተለያዩ ፕሮጀክቶች አማካኝነት የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ነው፡፡
ከአትሌቲክስ ስኬቱ ባሻገር በ2020 በስሙ ባቋቋመው ፋውንዴሽን በተለይም ትምህርት ቤቶችንና ቤተመጻሕፍትን በመገንባት እንዲሁም ጥብቅ ደኖችን በማልማት ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፡፡
ኪፕቾጌ ከ41 ዓመት በፊት ነበር ልክ በዛሬዋ ቀን በደቡብ ምዕራብ ኬንያ ናንዲ ግዛት ካፕሲስዋ የተወለደው፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ

