Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በምክክር እና በሰጥቶ መቀበል መርህ ምላሽ ማግኘት አለበት – ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ያነሳችው የባህር በር ጥያቄ በምክክር እና በሰጥቶ መቀበል መርህ ምላሽ ማግኘት አለበት አሉ ምሁራን።

የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ብሩክ ኃይሉ (ፕ/ር) ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ለሺህ ዓመታት የባሕር በር ያለን ሀገር በ30 ዓመታት አጭር ታሪክ ምክንያት የባሕር በር አጥተን አንቀርም ብለዋል።

ብሩክ ኃይሉ (ፕ/ር)

ባለፉት ዘመናት መርከቦቻችን በየአቅጣጫው ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ያደርጉ ነበር ሲሉ አስታውሰዋል።

ቀደምት የባህር በር ባለቤቷ ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር መመለሷ አይቅርም ያሉት ብሩክ (ፕ/ር)፤ የባሕር በር ጥያቄያችንን ለመመለስ ሰላማዊ ጥረታችንን አጠናክረን ቀጥለናል ብለዋል።

ኢህአዴግ ጥያቄው አይመለከተንም በሚል ጉዳዩን በሚያሳዝን ሁኔታ ወደ ጎን ብሎት እንደነበር አስታውሰው፤ በድርድር ወቅት የአሰብ ጉዳይ ላይ አለመፈለግ የታየው ከእኛው ልዑክ ነበር ሲሉ ገልጸዋል።

ከለውጡ ወዲህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት እንመካከር፣ በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንደግ፣ በጋራ የሰጥቶ መቀበል መርህ እንስራ የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ መቅረቡን አንስተዋል።

ነገር ግን በአስመራ መንግስት በኩል ለጉዳዩ ትኩረት ለመስጠት ፍላጎት ያለመኖሩን የገለጹት ብሩክ (ፕ/ር)፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ከኢትዮጵያውያን በላይ ማንም እንደሌለ አስገንዝበዋል።

ቀይ ባሕር ላይ ሀገራት ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው ብሔራዊ ጥቅማቸውን እንደሚያስከብሩ ገልጸው፤ በቀጣናው የምንገኘው እኛ ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስጠበቅ መስራት አለብን ብለዋል።

አበበ ከበደ (ዶ/ር)

የዓለም የተፈጥሮ ኃብትና የአካባቢ ጥበቃ የሕግ ባለሙያ የሆኑት አበበ ከበደ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ እያነሳች የሚገኘው የባሕር በር ጥያቄ ተፈጥሯዊ እና ሕጋዊ መሆኑን ገልጸዋል።

ያለፉት መንግስታት የተሳሳቱትን ስህተት የማረም ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸው፤ አዳዲስ ተራማጅ እሳቤዎችን ለማስረጽ የሚሰራው ስራ ውጤት እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።

የባሕር በር ጥያቄውን ለመመለስ የሚያስችሉ ተግባራዊ እርምጃዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ነው ያመለከቱት።

የጀመርነው የልማት፣ የእድገት እና የብልጽግና ጉዞ በርካታ ወደቦች እንደሚያስፈልጉን አመላካች ነው ያሉት አበበ (ዶ/ር)፤ የተሰሩ ስሕተቶችን ማስተካከል እና የባህር በር ጥያቄያችንን መመለስ አለብን ብለዋል።

ኢትዮጵያ የወደብ አማራጭ የምታገኝባቸውን መንገዶች በመፍጠር ቀጣናዊ የጋራ እድገት እና ልማት ማጎልበት ይጠበቅባታል ነው ያሉት።

በዮናስ ጌትነት

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

Exit mobile version