አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጤና ሚኒስቴር የህክምና ኦክስጂን እጥረት ለመፍታት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው አለ።
በሚኒስቴሩ የጤና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ተገኔ ረጋሳ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ መንግስት በሽታን አስቀድሞ ከመከላከል ባለፈ አክሞ ማዳንን የፖሊሲው አካል አድርጎ እየሰራ ይገኛል።
ከዚህ በፊት በዘርፉ የሚያጋጥመውን የህክምና ኦክስጂን እጥረት ለመፍታት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ አሁን ላይ 58 ሆስፒታሎች የህክምና ኦክስጂን ማምረት መቻላቸውን ተናግረዋል።
ታማሚዎች በራሳቸው መተንፈስ በማይችሉበት ወቅት ለመተንፈስ የሚረዳቸው ማሽን በ177 ሆስፒታሎች መኖሩን አንስተው÷ ታካሚዎች የተሳለጠ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዮሐንስ ሃ/ሚካኤል የህክምና ኦክስጂንን በራስ አቅም ማምረት መቻሉ ለታካሚዎች የሚሰጠውን አገልግሎት የተቀላጠፈ እንደሚያደርገው አስረድተዋል።
ሆስፒታሉ የመተንፈሻ አካባቢ ታካሚዎችን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያስተናግድ በመሆኑ ቀደም ባሉ ጊዜያት የህክምና ኦክስጂን ፍጆታው ከፍ ያለ እንደሆነና አሁን ላይ ሆስፒታሉ ኦክስጂን ማምረት በመጀመሩ ፍላጎቱን ለማሟላት ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።
በዚህም 60 በመቶ የሚሆነውን የህክምና ኦክስጂን ፍላጎት በራሱ አቅም ማምረት እንደጀመረ ገልጸዋል።
በሶስና አለማየሁ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

