Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመዲናዋ 36 ሺህ 600 ዜጎችን በየቀኑ የሚመግቡት ማዕከላት…

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከላት 36 ሺህ 600 ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል አለ የከተማ አስተዳደሩ ምገባ ኤጀንሲ፡፡

የኤጀንሲው ም/ዋና ዳይሬክተር ስንታየሁ ማሞ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ ተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ለማሕበራዊ ችግር ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው፡፡

በዚህም መሰረት በመዲናዋ ከፍተኛ ድጋፍ የሚሹ የሕብረተሰብ ክፍሎች በቀን አንዴ በማዕከላቱ የምገባ አገልግሎት እያገኙ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ በከተማዋ 26 የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከላት መኖራቸውን ጠቁመው ÷ በማዕከላቱም 36 ሺህ 600 ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል ነው ያሉት፡፡

በቀጣይ አገልግሎቱን ለማጠናከር እየተሰራ ነው ያሉት ም/ዋና ዳይሬክተሯ ÷ ለዚህም ባለሃብቶችና አጋር አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

ማዕከላቱ ከምግባ ባሻገር የሥራ እድል እየፈጠሩ መሆኑን ጠቁመው ÷ ከ350 በላይ እናቶች የሥራ እድል ማግኘታቸውን አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል 500 የምገባ ተጠቃሚዎችን የክህሎት ሥልጠና በመስጠት ራሳቸውን እንዲችሉ መደረጉን ነው የገለጹት፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version