አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 13 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የማሊው ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ቡባካር ኬዬታ በትናንትናው ዕለት በሀገሪቱ ወታደሮች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ፕሬዚዳንቱ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በሀገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ባስተላፉት መልዕከት ስልጣን መልቀቃቸውን በመግለፅ ፓርላማው መበተኑን አስታውቀዋል።
በሀገሪቱ ባለው ሙስና እና በተዳከመ የፀጥታ ጉዳዮች ምክንያት ከፍተኛ ተቃውሞ ሲነሳባቸው የቆዩት ፕሬዚዳንቱ በሀገሪቱ ወታደሮች በመኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ነው ከስልጣን መልቀቃቸውን ይፋ ያደረጉት።
ፕሬዚዳንቱ እኔ በስልጣን እንድቆይ ደም ሊፈስ አይገባም ብለዋል ባስተላለፉት መልዕክት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቡቡ ሲሴ እና ፕሬዚዳንቱ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በዋና ከተማዋ አቅራቢያ ወደሚገኝ ወታደራዊ ጣቢያ መወሰዳቸውን የአልጀዚራ እና ቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።
መሪዎቹን በቁጥጥር ስር ያዋሉት ወታደሮቹ ስልጣን ለመያዝ ፍላጎት እንደሌላቸው የገለፁ ሲሆን ሀገሪቱን የማረጋጋት ስራ እንደሚሰሩ ግን ገልጸዋል።
ሆኖም የአፍሪካ ህብረት፣ የማሊ የቀድሞ ቅኝ ገዥ ፈረንሳይ እና የአካባቢው ሀገራት የወታደሮችን እርምጃ ተቃውመውታል።

