አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 13 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጥፋት ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 32 የኦነግ ሸኔ አባላት ከእነ ሙሉ ትጥቃቸው በምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ እጃቸውን ለመንግስት ሰጡ፡፡
አባላቱ ኦሮሞን ነጻ እናውጣ በሚል ሽፋን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን የመግደል፣ የህዳሴውን ግድብ የማደናቀፍና ሌሎች የመሰረተ ልማት ተቋማትን የማጥቃት ተልዕኮ ተቀብለው እንደነበር ገልጸዋል፡፡
እጃቸውን ከሰጡ የኦነግ ሸኔ አባላት መካከል አቶ ገልማ ቡሌ በትግል ስም ዲናራሳ የተባሉት የጥፋት ተልዕኮውን ለማሳካት ወታደራዊ ስልጠና መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡
የጥፋት መንገድን በመከተል የክልሉን ህዝብ ነጻ ማውጣት እንደማይቻል በመገንዘብ፣ ችግርም ካለ በውይይትና ድርድር በመፍታት በሰላማዊ መንገድ ለመታገል እጃቸውን እንደሰጡ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ሸኔን ሽፍታ እንኳን አልልም፤ ሽፍታ ቢያንስ ስም አለው የሚሉት አቶ ገልማ፤ “ሽፍታ ተዋግቶ ገድሎ ይሞታል፤ የሸኔ ፍላጎት ግን የሌብነትና ወንድምን ከወንድም የማጋጫት ተግባር ነው” ብለዋል።
ለዚህም “ከህወሃት ጋር አብረው እያደረጉ ያሉ እንጂ ለምንም ስልጣን እየተፋለሙ እንዳልሆነና ለዝርፊያ እየተሯሯጡ ያሉ ናቸው” ሲሉም ገልጸዋል።
ሌላው አባል አበበ ጂሎ በትግል ስም አብዲ ሰባ የተባለው ደግሞ ‘ኦሮሞ ተበድሏል’ በሚል ተታሎና ወታደራዊ ስልጠና ወስዶ ለጥፋት ተልዕኮ ኦነግ ሸኔን እንደተቀላቀለ ተናግሯል፡፡
የኦነግ ሸኔ ዓላማ የሰው ህይወት ማጥፋት፣ መዝረፍና በመሰረተ ልማት ላይ ጉዳት ማድረስ በመሆኑ በዚህ ተግባር መቀጠል ስላልፈለኩ እጀን ለመንግስት ሰጥቻለሁ ብሏል፡፡
ሌላው ኣጋ አረቦ በትግል ስም ቄራንሶ ሰባ የኦነግ ሸኔ የትግል ስልትና ዓላማ ከኦሮሞ ባህላዊ ስርዓት ያፈነገጠና የክልሉን ህዝብ የማይመጥን በመሆኑ ወደ ሰላማዊ ህይወት ተመልሻለሁ ነው ያሉት፡፡
የሰው ህይወት እያጠፉና የመሰረተ ልማትን እያወደሙ ለኦሮሞ ህዝብ እታገላለሁ ማለት ራስን ማታለል ስለሆነ ከዚህ በኋላ ዳግም እንደማይሳሳትና እንደማይቀበሉትም ነው የተናገሩት፡፡
አቶ አጋ አክለውም “ቡራቡሬ ልብስ ለብሶ ይመጣና እኛ ነን መንግስት ይላል፤ ባርነት ስር ነበራችሁ፤ ዛሬ ግን ነጻነታችሁን እናጎናጽፏችኋለን፤ ወደ እኛ ተመለሱ ብዙ ነገር እናደርግላችኋለን፣ ሀገራችሁን እንዳትለቁ አድርገን በደንብ እናሰለጥናችኋለን ይላሉ፤ ይህን አምነን ከገባንበትና ከሰለጠንን በኋላ ተመልሶ መንግስት ሲዘርፋችሁ ሲበዘብዛችሁ የቆየ መንግስት ነው አሉን፤ ጦርነት ከሶማሌ ይነሳል፤ ከአባይም ይነሳል፣ በዚያ ጊዜ እናንተ እዚሁ ታጣቂዎችን ትዋጋላችሁ አሉን። እንዲህ በማለት እኛን ካስገበረን በኋላ የልቡን ማድረግ ፈልጎ ነው።” ብለዋል።
የኦሮሞ አባ ገዳዎችና ቃሉዎች ኦነግ ሸኔ ሰላማዊ የትግል አማራጭ እንዲከተል ጥያቄ አቅርበው እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
የምዕራብ ጉጂ ዞን አስተዳደሪ አቶ ተፈሪ ወንድይፍራው በኦሮሞ ህዝብ ስም ጫካ መሽጎ የሰው ህይወት የሚያጠፋ፣ ንብረት የሚዘርፍና የመሰረተ ልማት ላይ ጉዳት የሚያደርስን ሃይል እንደማይታገሱ አስታውቀዋል፡፡
በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በኦነግ ሸኔ ተመልምለው በህዝብ ላይ ጥፋት ሲፈጽሙ የነበሩ ወገኖች ዓላማው ሲገባቸው ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለስ መጀመራቸውንም ገልጸዋል፡፡

