Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓልን ስናከብር ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 20ኛዉን የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓልን ስናከብር የሁሉንም ዜጋ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ነው አሉ በሚኒስትር ማዕረግ የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ወ/ሮ እናትዓለም መለሰ።

20ኛዉ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል ‘ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት’ በሚል መሪ ቃል ይከበራል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በተገኙበት የበዓሉን መሪ ቃል አስመልክቶ በዛሬዉ ዕለት የትንተና መድረክ ተካሂዷል።

በዚሁ ወቅት ወ/ሮ እናትዓለም መለሰ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያውያን በዓሉን ሲያከብሩ ሃሳባቸውን በመለዋወጥ ለጋራ ዕድገታቸው ይዘምታሉ።

20ኛውን የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓልን ስናከብር የሁሉንም ዜጋ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ነው በማለት ገልጸው፤ በዓሉ የኢትዮጵያውያንን አንድነት በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻ እና የሃብት ባለቤት መሆኗን አንስተው፤ በዓሉ ሲከበር ሀብታችንን በሚገባ ማስተዋወቅ አለብን በማለት አፅንኦት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያውያን በትብብር ሰርተን ሀገራዊ ብልፅግናን በማረጋገጥ ለአፍሪካ ተምሳሌት መሆን አለብን ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ አንገቱን የማይደፋ እና ለልመና እጁን የማይዘረጋ ትውልድ እየገነባች ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።

20ኛዉ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት በሆሳዕና ከተማ ሕዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም ይከበራል።

በወንድማገኝ ጸጋዬ

Exit mobile version