Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለኢትዮጵያ የደን ልማት የፋይናንስ ድጋፍ ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት አግዛለሁ – ፋኦ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2 ፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ኢትዮጵያ በደን ልማት ለምታከናውናቸው ተግባራት የፋይናንስ ድጋፍ ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት አግዛለሁ አለ፡፡

የፋኦ የኢትዮጵያ ተወካይ ፋራይ ዚሙድዚ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያ ደኖችን መልሶ በማልማትና በመንከባከብ ረገድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባከናወነቻቸው ሰፋፊ ስራዎች መሻሻሎች ታይተዋል፡፡

በዚህም ዓለም አቀፍ የካርቦን ፋይናንስ ድጋፍ ለማግኘት ወሳኝ ሂደት ማለፏን ጠቁመው፥ ፋኦ ይህንን ጥረት እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል፡፡

የካርቦን የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ወሳኝ በሆኑት የደን ጥበቃና የመሬት መራቆትን በመቀነስ ረገድ ኢትዮጵያ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች ለማረጋገጥ ተቋማቸው ከኢትዮጵያ የደን ልማት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ድጋፉ በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ይበልጥ ተጎጂ የሆኑ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸው፥ በዚህ ረገድ የተከናወኑ ተግባራት ከፋይናንስ ድጋፍ ባሻገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባሻገር የረዥም ጊዜ የኢኮኖሚና አካበቢያዊና ጠቀሜታን በሚያረጋግጥ መልኩ ዘላቂ የደን ልማት አስተዳደርን እየተገበረች መሆኗን አንስተዋል፡፡

ፋኦ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን የመቋቋም አቅምን በመገንባት፣ የተራቆቱ የመሬት ገጽታዎችን ወደነበሩበት በመመለስና ዘላቂ የደን አስተዳደርን በማረጋገጥ ረገድ የኢትዮጵያ ቁልፍ አጋር ሆኖ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

Exit mobile version