Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢንሳ የአይ ኤስ ኦ 9001፡2015 ዓለም አቀፍ የጥራት ሥራ አመራር እውቅና አገኘ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) የጥራት መስፈርቶችን በማሟላት የአይ ኤስ ኦ 9001:2015 ዓለም አቀፍ የጥራት ሥራ አመራር ስርዓት ማረጋገጫ እውቅና ተሰጥቶታል፡፡

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ የጥራት ሥራ አመራር ስርዓት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀቱን በይፋ ተረክበዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ተቋሙ በሳይበር ኢንዱስትሪ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዎንታዊ ተፅዕኖ ለመፍጠር በሚሰጣቸው አገልግሎቶች የጥራት ልህቀትን ለማረጋገጥ የጥራት አስተዳደር ስርዓትን ተግባራዊ አድርጓል፡፡

እውቅናው ተቋሙ ለጥራት በሚሰጠው ትኩረት የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት እንዳልሆነ ገልጸው፥ ተደራሽ ለምናደርጋቸው ምርቶችና አገልግሎቶች ሁሉንም የቁጥጥር፣ የህግና የደንበኞችን ፍላጎት ይበልጥ ለማሻሻል ወሳኝ እጥፋት ላይ እንዳለን አመላካች ነው ብለዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ እውቅናው ተቋሙ ሀገራዊ ተልእኮውን በብቃት እንዲወጣ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር መአዛ አበራ (ኢ/ር)፥ ኢንሳ የጥራት አስተዳደር ስርዓት አስፈላጊ መስፈርቶችን በአግባቡ በመተግበሩ እውቅናው እንደተሰጠው ገልጸዋል፡፡

እውቅናው የአሰራር ሂደቶችን በማሻሻል፣ ቅልጥፍናን በማሳደግ፣ ሀገራዊ የሳይበር ደህንነትን የማረጋገጥ አቅሙን በማሳደግ፣ አገልግሎቶቹን የደንበኞችን ፍላጎት በሚያሟላ መልኩ ለመስጠት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ተቋም እንዲሆን የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያ በዚህ የዓለም አቀፍ የጥራት ሥራ አመራር ስርዓት ትግበራ ሂደት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦች እውቅና መሰጠቱን ተቋሙ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

Exit mobile version