አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የኢንዱስትሪ ልማትን ለማጠናከርና የስራ እድል ፈጠራን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፡፡
በደብረ ብርሃን ከተማ የብራውን ፉድስ የበቆሎ ማቀነባበሪያ እና የምግብና የእንስሳት መኖ ማምረቻ ፋብሪካ ተመርቋል፡፡
አቶ አረጋ ከበደ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ፋብሪካው በግብርና ዘርፍ የሚመረቱ ግብዓቶችን የሚጠቀምና የበለጸገ የምግብ አቅርቦትን የሚያሳድግ ነው።
ፋብሪካው የክልሉ መንግስት የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማሳደግ የያዘው ፖሊሲ አካል መሆኑን ገልጸው÷ ከስራ እድል ፈጠራና ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር ሰፊ አበርክቶ እንዳለው ተናግረዋል።
የብራውን ፉድስ ፋብሪካ እንደሀገር ያለውን የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ትግበራን የሚደግፍ መሆኑን አመላክተዋል።
የክልሉን አጠቃላይ ልማት ለማሳደግ ሕዝቡ ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ በሳል አመራር መስጠት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በለይኩን ዓለም

