አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የሚሰጠው የምገባ አገልግሎት ለተማሪዎች አዕምሯዊና አካላዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው አለ የከተማ አስተዳደሩ ምገባ ኤጀንሲ፡፡
የኤጀንሲው ም/ዋና ዳይሬክተር ስንታየሁ ማሞ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ አሁን ላይ በአዲስ አበባና ሸገር ሲቲ ከተሞች በሚገኙ ከ800 በላይ ት/ቤቶች የምገባ አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡
በዚህም ባለፉት ሶስት ወራት ከ976 ሺህ 700 በላይ ተማሪዎችን የት/ቤት ምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ለተማሪዎች የተመጣጠኑ ምግቦችን በማቅረብ አዕምሯዊና አካላዊ እድገታቸው የተሻለ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በቀን ሁለት ጊዜ የሚሰጠው የምገባ አገልግሎቱ ከቅድመ መደበኛ እስከ 8ኛ ክፍል የሚገኙ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በተገቢ ሁኔታ እንዲከታተሉ በማድረግ የመቅረት ምጣኔን ቀንሷል ነው ያሉት፡፡
በሌላ በኩል ከተማ አስተዳደሩ ለተማሪዎች ዩኒፎርም እና ሌሎች የመማሪያ ቁሳቁስ ግብዓት ተደራሽ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡
ከተማሪዎች ምገባ አገልግሎት ጋር ተያይዞ ከ16 ሺህ በላይ ለሚሆኑ እናቶች የሥራ እድል መፈጠሩን ም/ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል፡፡
“ለተማሪዎች እፎይታ እስከ ትውልድ ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ የሚሰጠውን የት/ቤት ምገባ አገልግሎት ይበልጥ ለማጠናከርም ባለሃብቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በመላኩ ገድፍ

