አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የእንግሊዝ ባህል እና እግር ኳስ ልዩ መለያ – ሰር ዴቪድ ጆሴፍ ቤካም፡፡
ትውልዱ በፈረንጆቹ 1975 በእንግሊዝ ዋና ከተማ ለንደን የሆነው ዴቪድ ቤካም የእንግሊዝ እግር ኳስ እና ባህል ልዩ መለያ ነው፡፡
የቀድሞ አማካይ በአራት የተለያዩ ሀገራት ሊጎች በመጫወት ዋንጫዎችን ያሸነፈ ብቸኛው እንግሊዛዊ ተጫዋች ነው፡፡
በአስደናቂ ኳስ የማቀበል ችሎታውና በተሸጋሪ ኳሶቹ እንዲሁም የቆሙ ኳሶችን በማስቆጠር ብቃቱ ይበልጥ የሚታወቀው ዴቪድ ቤካም የትውልዱ ኮከብ እንደነበር ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡
20 አመታትን ባሰላፈበት እግር ኳስ በክለብ ደረጃ 19 ዋንጫዎችን መሰብሰብ የቻለ ሲሆን፥ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ፣ በስፔን ላሊጋ፣ በፈረንሳይ የሊግ አንድ እና በአሜሪካ ሜጀር ሊግ ሶከር ዋንጫዎችን ማሳካት የቻለ ብቸኛው እንግሊዛዊ ተጫዋች ነው፡፡
የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ህይወቱን በፈረንጆቹ 1992 በማንቼስተር ዩናይትድ የጀመረው ቤካም ከቡድኑ ጋር ስድስት ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ሲሆን፥ ሁለት የኤፍ ኤ እና አንድ የሻምፒየንስ ሊግን ዋንጫን ጨምሮ በርካታ ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡
ከማንቼስተር ዩናይትድ ወደ ስፔኑ ሀያል ክለብ ሪያል ማድሪድ ከተዘዋወረ በኋላ ለሎስ ብላንኮዎቹ በተጫወተባቸው አራት ዓመታት የላሊጋውን ዋንጫን ማሳካት ችሏል፡፡
በፈረንጆቹ 2007 ታሪካዊና ለአሜሪካ እግር ኳስ ብስራት ነው የተባለለትን ዝውውር ወደ ሜጀር ሊግ ሶከር ተሳታፊው ኤል ኤ ጋላክሲ በማድረግ በክለቡ ቆይታው በ2011 እና 2012 ሁለት ጊዜ የሊጉን ዋንጫ አንስቷል፡፡
ሆኖም በመሃል በ2009 እና በ2010 የውድድር ዓመታት በሁለት የተለያዩ የውሰት ውሎች ለጣሊያኑ ክለብ ኤሲ ሚላን ተጫውቷል፡፡
ከኤል ኤ ጋላክሲ ወደ ፈረንሳዩ ክለብ ፓሪሴን ዠርማ በመዘዋወር ለአራት ወራት የተጫወተ ሲሆን፥ ከክለቡ ጋር የፈረንሳይ ሊግ አንድ ዋንጫን አሳክቷል፡፡
ለሀገሩ እንግሊዝ 115 ጨዋታዎችን ያደረገው ዴቪድ ቤካም 17 ግቦችን ሲያስቆጥር፥ ብሔራዊ ቡድኑን ለስድስት አመታት በአምበልነት መርቷል፡፡
ከ20 አመታት የእግር ኳስ ተጫዋችነት ቆይታው በኋላ በፈረንጆቹ 2013 ጫማ ሰቅሏል፡፡
የእግር ኳስ ተጫዋችነት ጉዞውን ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ፋሽን ኢንዱስትሪው በስፋት ፊቱን ያዞረ ሲሆን፥ በአሜሪካው ክለብ ኢንተር ማያሚ እና በሀገሩ ሳልፎርድ ሲቲ የባለቤትነት ድርሻ አለው፡፡
ከአንጸባራቂ የእግር ኳስ ህይወቱ በተጨማሪ የእንግሊዝ ባህል ልዩ መገለጫ እንደሆነ የሚነገርለት ዴቪድ ቤካም በበጎ አድራጎት ስራዎቹም በስፋት ይታወቃል፡፡
የ50 አመቱ ዴቪድ ቤካም በስፖርቱና በበጎ አድራጎት ስራዎቹ በሰራው ታላቅ ስራ በእንግሊዝ ትልቅ ክብርና ቦታ የሚሰጠውን ‘ሰር’ የሚለውን ማዕረግ በቅርቡ ከብሪታንያ ንጉስ ቻርለስ ተቀብሏል፡፡
በአቤል ነዋይ

