አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሄሞራጂክ ፊቨር በሽታ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጅንካ ከተማ ተከስቷል አለ የጤና ሚኒስቴር፡፡
ሚኒስቴሩ ወቅታዊ የጤና ጉዳይን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው÷ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን አደጋዎች እንዳይከሰቱ የመከላከልና ከተከሰቱም በአፋጣኝ የማረጋገጥና የተቀናጀ የቅኝትና የምላሽ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
በዚህም በአሁኑ ወቅት በደቡበ ኢትዮጵያ ክልል ጅንካ ከተማ ምንነቱ በመረጋገጥ ላይ ያለ የሄሞራጂክ ፊቨር በሽታ መከሰቱን የቅኝት መረጃዎች ማመላከቱን አስታውቋል።
በበሽታው እስካሁን ስምንት ሰዎች መጠርጠራቸውንም አመላክቷል።
የጤና ሚኒስቴር የበሽታው መንስኤን ለማወቅ እና ተጨማሪ ስርጭትን ለመግታት እንዲሁም ለመቆጣጠር ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን ወደ ቦታው በመላክ የመስክ ግምገማዎች እና የላብራቶሪ ምርመራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም የማህበረሰብ ቅኝት፣ የንክኪ ልየታ፣ የቤት ለቤት ልየታ እንዲሁም የህክምና አገልግሎት አሰጣጥን እያጠናከረ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በመሆኑም ሚኒስቴሩ ሌላ ተጨማሪ መግለጫ እስከሚሰጥ ድረስ ለመከላከል የሚከተሉትን ምከረ ሐሳቦች እና ጥንቃቄዎች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
👉 በአፍ፣ አፍንጫ እና ሌሎች የሰውነት ከፍሎች የመድማት፣ትኩሳት፣ማስቀመጥ እና ማስመለስ ምልክት ሲኖር ወደ ህክምና ተቋማት መሄድና በወቅቱ የላቦራቶሪ ምርመራ ማድረግ፣
👉 ምልከት ከታየበት ማንኛዉም ሰዉ ጋር ንክኪ በሚኖርበት ጊዜ ራስን የመከላከያ ዘዴዎችን መጠቀም፣
👉 ሁልጊዜ እጅን በሳኒታይዘር ወይም በውሃና በሳሙና በመታጠብ ማጽዳት፣
👉 ማንኛውም ጤና ተቋም በታካሚዎች ልየታ አካባቢ ልዩ ትኩረት በመስጠት የቫይራል ሄሞሬጅክ ፊቨር (Viral Hemmoragic Fever) መሰል በሸታ መለየት፣ መመርመር፣ ማከም እና ሪፖርት ማድረግ ያስፈልጋል ተብሏል።

