አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሰው ኃይል ልማትና ክህሎት ማበልፀግ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ያለንን ትብብር አጠናክረን እንቀጥላልን አሉ የልማት አጋሮች፡፡
ወጣቶች የተሻለ ዕውቀትና ክህሎት ታጥቀው የሥራ ገበያውን የሚቀላቀሉበትን አቅም የሚያሳድግ አዲስ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ ይፋ ሆኗል።
አዲሱ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ የክህሎት ተደራሽነትን በማስፋት ወጣቶች የተሻለ የሥራ ዕድል የሚያገኙበትን ምቹ ምኅዳር ለመፍጠር ያለመ ነው፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ አዲሱ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ ፍትሃዊነትንና ተደራሽነትን በማስፋት የስልጠና ጥራትን ለማስጠበቅ ወሳኝ ሚና አለው።
የወጣቶችን የሥራ ፈጠራ፣ የሥራ ገበያ፣ የዲጂታል ዕውቀትና ክህሎትን በማጎልበት ሁሉንም አጣጥሞ መምራት በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ ስትራቴጂ መሆኑን ገልጸዋል።
በስትራቴጂው ትግበራ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ባለድርሻ አካላትን ትብብር ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የኢትዮጵያን የዕድገት ጉዞ የሚያሳልጥ በዕውቀትና ክህሎት የዳበረ የሰው ሃይል የማፍራት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት የሰው ሀብት ልማት ፕሮግራም ኦፊሰር ኢቫ ጁኒየት በበኩላቸው÷ ህብረቱ በኢትዮጵያ ቅድሚያ ሰጥቶ ከሚያከናውናቸው ተግባራት አንዱ የክህሎት ልማት እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የክህሎት ልማት ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለኢንተርፕራይዝ ልማትና ለኢኖቬሽን ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቅሰው÷ አዲሱ ስትራቴጂ የግሉ ዘርፍና አጋር አካላት በትብብር እንዲሰሩ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሰው ሀብት ልማትን፣ ክህሎትንና እውቀትን ለማሳደግ ለምታከናውነው ጥረት ህብረቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ የልማት ትብብር አማካሪ አንጃ ፖልስ ÷ ሀገራቸው በታዳሽ ኃይል፣ በግብርና፣ አየር ንብረት፣ በቴክኒክና ሙያ ስልጠናና ሌሎች ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው ÷ ያለውን የልማት አጋርነት አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

