Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አባተ አበበ የተባለ ግለሰብን በመግደል ወንጀል የተከሰሰው ተስፋዬ ሆርዶፋ በ20 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አባተ አበበ የተባለ ግለሰብን በመግደል ወንጀል የተከሰሰው ተስፋዬ ሆርዶፋ በ20 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኗል።

የግራ ቀኝ ማስረጃን መርምሮ የቅጣት ውሳኔ ያሳለፈው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የግድያና የከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ነው።

የፍትህ ሚኒስቴር የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቢ ህግ ተስፋዬ ሆርዶፋ በተባለ ግለሰብ ላይ በከባድ ግድያ ወንጀል ማለትም የወንጀል ህግ አንቀጽ 539 ንዑስ ቁጥር 1ሀ እና የጦር መሳሪያ አዋጅ ቁጥር 1177/2012 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ የጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘት ሁለት ክሶችን መስርቶበት እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።

በዚህም ክስ ዝርዝሩ ላይ እንዳመላከተው ተከሳሹ ተስፋዬ ሆርዶፋ ከአዲስ አበባ ከተማ እና ከገላን ከተማ ፍቃድ ካወጣባቸው ሁለት የእስታር ሽጉጥና የማካሮቭ የጦር መሳሪያዎችን ውጪ በመንግስት ዕውቅና የሌለው ማለትም ፍቃድ ያልወጣበትን ሌላ ህገወጥ ሽጉጥ በተሽከርካሪው ውስጥ ደብቆ በመያዝ በታሕሣሥ 7 ቀን 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ ቦሌ ኤድናሞል አካባቢ ከምሽቱ 4:00 ላይ አባተ አበበ የተባለ ግለሰብን በ3 ጥይት በመምታት ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርጓል፡፡

በወቅቱም ህገወጥ ሽጉጡን በመያዝ አምልጦ እንደነበር እና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጥብቅ ክትትል በቁጥጥር ስር መዋሉ ተጠቅሶ ክስ ቀርቦበታል።

ዐቃቢ ህግ ከክሱ ጋር የሰው ምስክር ዝርዝርና የተለያዩ ገላጭና አስረጂ የፎረንሲክ ማስረጃዎችን አያይዞ አቅርቧል።

ተከሳሸ ችሎት ቀርቦ የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሰውና ክሱን በንባብ ከማሰማት በኋላ የወንጀል ድርጊት አለፈፀሙን ገልጾ የእምነት ክህደት ቃል መስጠቱን ተከትሎ ዐቃቢ ህግ የሰው ምስክሮችን አሰምቷል፡፡

ፍርድ ቤቱም የዐቃቢ ህግ ማስረጃዎችን መርምሮ በክሱ ላይ የተገለጸው ወንጀል መፈጸሙን በዐቃቢ ህግ ማስረጃ መረጋገጡን ጠቅሶ በተከሰሰበት በሁለቱም ድንጋጌዎች ስር እንዲከላከል ብይን ሰጥቷል፡፡

ተከሳሹ የተለያዩ የመከላከያ ማስረጃዎችን አቅርቦ አሰምቶ የነበረ ቢሆንም የዐቃቢ ህግ ማስረጃን በተገቢው መከላከል አለመቻሉ ተጠቅሶ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎበታል።

ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ያቀረበውን 3 የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በመያዝ በደረጃ 2 በእርከን 36 መሰረት ሁለቱም ክሶች ተጠቃሎ በ20 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

Exit mobile version