Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የክልሉን ሰላምና ጸጥታ በማረጋገጥ ሰፊ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው – አፈ ጉባዔ ፋጤ ሰርሞሎ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6 ፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ጸጥታን በማረጋገጥ ሰፊ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው አሉ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፋጤ ሰርሞሎ፡፡

አፈ ጉባዔዋ ለ20ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የተደረገውን ዝግጅትና በክልሉ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም በክልሉ ለሰላም እና ጸጥታ ችግር ለነበሩ የአደረጃጀት ችግሮች ምላሽ መስጠት መቻሉን አብራርተዋል፡፡

ክልሉ ከምስረታው ወዲህ የተለያዩ ልማቶችን በስኬት ማከናወኑን ጠቁመው ÷ ለአብነትም የገጠርና ከተማ ኮሪደር ልማት ሥራዎች፣ የሌማት ትሩፋት፣ የቱሪስት መስሕቦችን ማልማት እና ሌሎች ሥራዎችን ጠቅሰዋል፡፡

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች165 የኮሪደር ልማት ሥራዎች እንዲሁም በወራቤና ቡታጅራ ከተሞች የወንዝ ዳርቻ ልማት እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

የገጠር ኮሪደር ሥራ ለገጠር አካባቢዎች ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የተሻለ የአኗኗር ዘዬን እየሰጠ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡

በሌላ በኩል የሰብል ልማት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የስንዴ ክላስተርን ጨምሮ ምርቶችን ከኢንዱስትሪዎች ጋር የማስተሳሰር ሥራ ተከናውኗል ነው ያሉት።

የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ማስፋትና የቱሪዝም ልማት በክልሉ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል ናቸው።

ክልሉ ለ20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ሰፊ ዝግጅት ማድረጉንም አፈ ጉባዔ ፋጤ ሰርሞሎ ተናግረዋል፡፡

በሰለሞን በየነ

Exit mobile version