Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በተለያዩ ክልሎች የሚታየው የሰዎች እንቅስቃሴ ለኮቪድ19ኝ ስርጭት መስፋፋት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል- አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 13 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በተለያዩ ክልሎች የሚታየው የሰዎች እንቅስቃሴ ለኮቪድ 19ኝ ስርጭት መስፋፋት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርማሪ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት አስታወቁ።
 
ኮቪድ 19ኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ አፈፃፀም የሚከታተለው መርማሪ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት በመላ ሀገሪቱ አሁን ላይ ንፅህናንም ሆነ ርቀትን መጠበቅ ተዘንግቷል ይላሉ።
 
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትም በአዲስ አበባ የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች ተዘዋውሮ የተመለከተው ከዚሁ የተለየ አይደለም።
 
የወትሮው አብሮ መብላት መጠጣት፣ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን በጠባብ ክፍል ተፋፍጎ የመመልከት ልማድ የቀጠለባቸው ስፍራዎችም ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።
 
አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበትም በአጠቃላይ አዋጁ የቀረ የመሰለበት ሁኔታን እያስተዋልን ነው ይላሉ።
 
መንግስት ከአዋጁ መውጣት አስቀድሞ ትምህርት ቤቶችን ከመዝጋት አንስቶ በርካታ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ቢወስድም፤ ህዝቡ ግን በዚያ ደረጃ ችግሩን ተገንዝቦ መፈፀም ላይ በየጊዜው መንሸራተት እየታየበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
 
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈፃፀም እየቀነሰ ለመምጣቱ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የጤና ጠንቅ የሚሆኑ አካላትን እንዲቆጣጠሩ ሃላፊነት የተጣለባቸው የፀጥታ አካላት እንቅስቃሴ መዳከም ተጠቃሽ ነው።
 
በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች የክልል ከተሞች የወጡ መመሪያዎችን ማስተግበሩ ላይ መቀዛቀዝ ቢኖርም የፀጥታ አካላት በሚወስዱት እርምጃ ብቻ ግን ወረርሽኙን መቆጣጠር አይቻልም ነው የሚሉት።
 
ከዚህ አንጻርም ዋነኛው የመፍትሄ ቁልፍ ህብረተሰቡ መሆኑን ይናገራሉ።
ከዚህ ባለፈም በህግ ማስከበር ሂደት ውስጥ የፀጥታ አካላትን የቫይረሱን ተጋላጭነት የሚቀንሱ እርምጃዎችን እንዲወስድም አሳስበዋል።
 
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርዱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በየአካባቢያቸው የሚመለከቱትን የኮቪድ19 መከላከል ስራ እንዲገመግሙ መመሪያ ሰጥቷል።
 
በዚህ መነሻም መንግስት ሊወስደው የሚችለው እርምጃ ሊሻሻል እንደሚችል ተገልጿል።
እስከዚያው ግን ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር ተናቦ ወረርሽኙ የከፋ ቀውስ እንዳያመጣ በመደማመጥ መስራት እንደሚገባው አጽንኦት ሰጥተዋል።
 
በፋሲካው ታደሰ
Exit mobile version