Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የቼልሲ የልብ ምት ካይሴዶ …

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ በዚህ ወቅት አይነኬ ከሆኑ ተጫዋቾች መካከል ኢኳዶራዊው የመሐል ሜዳ ኮከብ ሞይሰስ ካይሴዶ አንዱ ነው፡፡

ሦስተኛ የውድድር ዓመቱን በቼልሲ እያሳለፈ የሚገኘው ካይሴዶ በክለቡ ጥሩ ጊዜ እያሳለፉ ከሚገኙ ተጫዋች መካከል ቀዳሚው ነው፡፡

በሀገሩ ኢኳዶር በሚገኘው ኢንዲፔንዴንቴ ዴል ቫሌ እግር ኳስን የጀመረው ካይሴዶ በዚህ ወቅት ዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ ምርጥ የተከላካይ አማካይ ተጫዋቾች ተርታ ተሰልፏል።

የ24 ዓመቱ ኮከብ ካይሴዶ የተቃራኒ ቡድንን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማቋረጥ እና የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ በቼልሲ ድንቅ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡

የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ ከፈረንሳዊው ኮከብ ኒጎሎ ካንቴ በኋላ የተመለከተው ድንቅ የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ሞይሰስ ካይሴዶ፤ በወቅቱ በዝውውር ገበያው በበርካታ ትልልቅ ክለቦች ቢፈለግም ቼልሲን ምርጫው በማድረግ በ100 ሚሊየን ፓውንድ መቀላቀሉ ይታወሳል፡፡

ካይሴዶ ከብራይተን ቼልሲን ሲቀላቀል የስምንት ዓመት ውል የፈረመ ሲሆን ለአንድ ተጨማሪ ዓመት የማራዘም አማራጭም ውሉ ላይ መካተቱ ይታወሳል፡፡

ከፈረንጆቹ 2020 ጀምሮ የኢኳዶር ብሔራዊ ቡድንን እያገለገለ የሚገኘው ካይሴዶ፤ ለብሔራዊ ቡድኑ 57 ጨዋታዎችን በማድረግ 3 ጎል ያስቆጠረ ሲሆን በኮፓ አሜሪካ እና በዓለም ዋንጫ ውድድር ሀገሩን ወክሏል፡፡

በትውልድ ከተማው በሙጄር ትራባጃዶራ መንደር ስኩብላንድ ሜዳዎች ላይ ኳስ እየተጫወተ ያደገው ካይሴዶ፤ በልጅነቱ ኢቫን ጉሬራ የተባለ አሰልጣኝ የእግር ኳስ ጫማ፣ የጉዞ እና የምግብ ወጪ ይረዳው ነበር፡፡

ካይሴዶ በፈረንጆቹ 2024 በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ለቼልሲ የመጀመሪያውን ጎል ከ50 ሜትር ርቀት ቦርንማውዝ ላይ ማስቆጠሩ አይዘነጋም፡፡

የቀድሞ የአርሰናል፣ ባርሴሎና እና ቼልሲ ተጫዋች ፈረንሳዊዉ ኢማኑኤል ፔቲት፤ ራሱን በሚገባ እያሻሻለ የሚገኘው ካይሴዶ ከሊጉ ምርጥ ተጫዋቾች ዉስጥ አንዱ ነዉ ሲል አሞካሽቶታል፡፡

በሊጉ ታሪካዊ ተጫዋች ለመሆን የግድ ዋንጫዎችን ማሳካት አለበት በእሱ ቦታ የተጫወቱ እነ ማኬሌሌ እና ካንቴ የተለያዩ ዋንጫዎችን ማሳካት ችለዋል ካይሴዶም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ አለበት ብሏል፡፡

ካይሴዶ ቼልሲን በተቀላቀለበት የመጀመሪያ የውድድር ዓመት በ35 የሊጉ ጨዋታዎች የተሰለፈ ሲሆን በሁለተኛ የውድድር ዘመኑ ደግሞ በሁሉም የሊጉ ጨዋታዎች በወጥነት ግልጋሎት ሰጥቷል፡፡

በ2022/23 የብራይተን የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠው ካይሴዶ በ2024/25 የውድድር ዓመት ደግሞ የቼልሲ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ መመረጡ ይታወሳል፡፡

ቼልሲ በ2024/25 የውድድር ዓመት ፒኤስጂን በማሸነፍ የዓለም ክለቦች ዋንጫን ሲያሳካ የሞይሰስ ካይሴዶ አስተዋፅኦ የሚተካ አልነበረም፡፡

አሁን ላይ ምርጥ ብቃታቸውን እያሳዩ ከሚገኙ የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ካይሴዶ የቼልሲ የልብ ምት መሆኑን በተደጋጋሚ እያሳየ ይገኛል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

Exit mobile version