Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

“ቦዮ ሐይቅ” የሀዲያ ዞን ተፈጥሯዊ ገጸ በረከት…

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀዲያ ዞን ተፈጥሯዊ ገጸ በረከት የሆነውን “ቦዮ ሐይቅ” የማልማት ሥራ ትኩረት እንደሚያስፈልገው ተመላክቷል።

20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን ለማስተናገድ የተዘጋጀው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለበዓሉ ያደረገውን ዝግጅት የሚዲያ ባለሙያዎች ምልከታ እያደረጉ ነው።

ጉብኝቱ በክልሉ የሚገኙ የቱሩዝም መደረሻ ሥፍራዎችን ያካተተ ሲሆን ÷ በሀዲያ ዞን የሚገኘው ቦዮ ሐይቅም ምልከታ ከተካሄደባቸው የተፈጥሮ መስህቦች ውስጥ አንዱ ነው፡፡

ከአዲስ አበባ በ230 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ቦዮ ሐይቅ ከሆሳዕና ከተማ በስተምስራቅ አቅጣጫ 54 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከቦኖሻ ከተማ ደግሞ በ5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

የቦዮ ሐይቅ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ በቆላማውና ለጥ ባለ ሜዳማው ሻሾጎ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን÷ በዞኑ ከሚገኙ ሐይቆች በስፋት ትልቁ ነው፤ በክረምት ወራት እስከ 6 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ይሸፍናል።

በጥልቀቱ እስከ 8 ሜትር እንደሚደርስ የሚገመተው ሐይቁ÷ ከስልጤ፣ ከምባታና ዙሪያው ከሚገኙ ወረዳዎች የሚነሱ ትልልቅ ገባር ወንዞች አሉት፡፡

ሐይቁ በውስጡ ባለው ደለል ምክንያት ጭቃማ ቢሆንም ከፍተኛ የሆነ የዓሣ ምርት ከመያዙ በተጨማሪ ለቱሪዝም ተመራጭ የሚያደርጉትን የዱር እንስሳትና አዕዋፋት በዙሪያው ይዟል። በተለይም የተለያዩ ሀገር በቀልና ስደተኛ አዕዋፋት ለሐይቁ ድምቀትና ውበት አጎናጽፈውታል፡፡

የሻሾጎ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ግርማ ሎቤ÷ ይህ የተፈጥሮ መስህብ ተገቢ ትኩረት አግኝቶ የጥበቃና የልማት ሥራ ከተሰራለት አካባቢው በቀላሉ ሊለማ የሚችል እንደሆነ ተናግረዋል።

ከልጅነት እስከ ዕውቀት “ከቦዮ ሐይቅ” የተዛመዱ የአካባቢው ነዋሪዎች ሐይቁ ለምቶና ጎብኚ ሲጎርፍበት ማየት የሁል ጊዜ ሕልማቸው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

አካባቢው ቢለማ እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት ማየት እንደሚቻል አስረድተዋል።

የመሰረተ ልማት እና ተደራሽነት፣ የሐይቁ ጥብቅና የአካባቢ አስተዳደር፣ የቱሪዝም ምርቶች ልማት እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ተጨምሮ አካባቢውን የተሻለ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራ የመሆን ዕድልን እንደሚሰጠው አመልክተዋል።

በሰለሞን በየነ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

Exit mobile version