አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተጠናከረ የፖሊስ ተቋም ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ደስታ ሌዳሞ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉን ፖሊስ ስልጠና ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት÷ ቁመናው የተስተካከለ ፖሊስ ለክልሉ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱ ለጀመረቻቸው ታላላቅ እሳቤዎች ወሳኝ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ሰላምና እድገት ያስፈልጋታል በማለት ገልጸው÷ ሀገሪቱን ወደ ነበረችበት ገናናነት ለመመለስ ዓላማ እና ፅናት ያለው የፖሊስ ተቋም አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ሰልጣኝ የፖሊስ አባላት ዓለም የደረሰበትን የፖሊስ ቴክኖሎጂዎች ሊላመዱና የኢትዮጵያን ወቅታዊ ብሔራዊ ፍላጎት በመረዳት ለተግባራዊነቱ ሊተጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተስፋዬ ዴቢሶ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ያለችበት ቀጣና ብዙ ፈተናና ተለዋዋጭ የፖሊቲካ ስርዓት ያለበት መሆኑን አንስተዋል፡፡
በተለዋዋጩ ቀጣናዊ ሁኔታ የሀገርን ጥቅም ለማስጠበቅ በሀገር አቀፍ ደረጃ የፖሊስ ተቋማትን ለማጠናክር እየተሰራ መሆኑን አንስተው÷ የክልሉን ፖሊስ ተቋም ስልጠናዎችን በመስጠት የአቅም ግንባታ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብልፅግና እንዲረጋገጥ የሲዳማ ፖሊስ የአካባቢውን ሰላም ከማስጠበቅ ጀምሮ ለማናቸውም ሀገራዊ ግዳጅ ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በጥላሁን ይልማ

