Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በአፍሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪ ለማድረግ እየተሰራ ነው – ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ለዓለም አቀፍ ለውጦች ምላሽ የሚሰጥና በአፍሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪ ለማድረግ እየተሰራ ነው አሉ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)፡፡

ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) የዩኒቨርሲቲውን 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓልን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት÷ በዓሉ ተቋሙ በ75 ዓመታት ውስጥ ያደረጋቸውን ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አስተዋጽዖ በመዘከርና ቀጣይ ስራዎችን በመተለም ይከበራል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ከሆነ ወዲህ የልህቀት ማዕከልነቱን ለማስጠበቅ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸው÷ የህግ ማዕቀፎችን መቀየር፣ ነፃነትና ተጠያቂነት ያለውን ፖሊሲ የማዘጋጀት ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም የአካዳሚ ፕሮግራም ማካሄድና ፕሮግራሞችን የማጣመር ስራዎች መሰራታቸውን አንስተው÷ በቀጣይ በምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ አቅም በመፍጠር እንዲሁም ፈፃሚ ባለሙያዎችን በማፍራት የራሱን ሚና እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለዓለም አቀፋዊ ለውጦች ምላሽ የሚሰጥና በአፍሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪ  እንዲሆን እየተሰራ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

በዓሉ ”ያለፈውን ማክበር የተሻለን ነገ ለማየት” በሚል መሪ ሐሳብ እንደሚከበርም ነው የተገለጸው።

በዙፋን አምባቸው

Exit mobile version