Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

7ኛው የአፍሪካና አውሮፓ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ በመጪው ሰኞ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛው የአፍሪካ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ በአንጎላ ሉዋንዳ ይካሄዳል፡፡

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ÷ የሁለቱ ተቋማት አጋርነት 25 ዓመታትን እንዳስቆጠረ አስታውሰዋል።

በባለ ብዙ ወገን ጉባዔው ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ አመራሮች፣ የህብረቱ ሀገራት መሪዎች፣ የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት እና ሌሎች የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ይታደማሉ፡፡

ሰላም፣ ደህንነት፣ የኢኮኖሚ ትስስር፣ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ የማይበገር የአየር ንብረት ለውጥ መገንባትና የሰው ኃይል ልማት የመርሐ ግብሩ አጀንዳዎች ናቸው፡፡

በአፍሪካ ህብረት የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ዣቪየር ኒኖ በበኩላቸው ÷ ጉባዔው የአፍሪካ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት የጋራ ጉዳዮች ላይ በትኩረት ለመምከር ያለመ ነው ብለዋል።

በአጀንዳ 2063 ዘላቂ የልማት ግቦች እንዲሁም የአፍሪካ ህብረትና የአውሮፓ ህብረት የ2030 የጋራ ራዕይ ላይ ምክክር እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡

የተቋማቱ መሪዎች ለባለብዙ ወገን ትብብር፣ አጋርነትና እያጋጠሙ ላሉ ፈተናዎች ምላሽ ለመስጠት የጋራ ቁርጠኝነታቸውን የሚያረጋግጡበት እንደሚሆንም አንስተዋል።

ወጣት መሪዎች፣ የሲቪክ ማሕበረሰብ ተቋማትና የግሉ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት የሚያነሷቸው ሃሳቦች በመሪዎች ጉባዔ ላይ እንደሚቀርቡ በመግለጫው ተመላክቷል።

በየሻምበል ምህረት

Exit mobile version