አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 13፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የመዲናዋ ምክትል ከንቲባ በመሆን የተሾሙት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ላለፉት ሁለት ዓመታት በምክትል ከንቲባነት ካገለገሉት ኢንጂነር ታከለ ኡማ ሀላፊነቱን ተረክበዋል።
በከንቲባ ፅህፈት ቤት በተካሄደ የስራ ርክክብ ስነ ስርዓት ላይም የስራ ኃላፊዎቹ በአዲስ አበባ አጠቃላይ የሥራ ሂደት ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
ከሰዓቱን ደግሞ ትናንት በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የማዕድን እና ነዳጅ ሚንስትር ሆነው የተሾሙት ኢንጂነር ታከለ ኡማ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመገኘት ከተቋሙ የቀድሞ ሀላፊ ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ የስራ ርክክብ አድርገዋል።
የሚንስቴሩ ሠራተኞች እና ሃላፊዎችም ለኢንጂነር ታከለ ኡማ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ኢንጂነር ታከለ የማዕድን ዘርፍ በሃገር በቀል የኢኮኖሚ እሳቤ ትልቅ ቦታ ያለው መሆኑን በዚሁ ወቅት አንስተዋል።
የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝት አንዱ አለኝታ እንደመሆኑም ዘርፉን ለማነቃቃት እና ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰሩ ነው ቃል የገቡት።
በዘርፉ ፍትሃዊነትን ማስፈን፣ ለወጣቶች ስራ መፈጠር እና ፕሮጀክቶች በአግባቡ እንዲመሩ ማስቻል ዋና ትኩረታቸው እንደሚሆንም ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተናግረዋል።
በዳዊት መስፍን

