Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሩጫ በኢትዮጵያ ትልቅ ታሪክና ቦታ አለው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

‎አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሩጫ በኢትዮጵያ ትልቅ ታሪክና ቦታ አለው አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

ከንቲባዋ ይህን ያሉት ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ዘርፍ ሁለት እውቅናዎችን ከዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ማሕበር ባገኘችበት መድረክ ነው።

የእውቅና ሥነ ሥርዓቱ በብሔራዊ ሙዚየም የተከናወነ ሲሆን÷ ኢትዮጵያ እውቅናውን ያገኘችው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እና አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ ለነበረው ሚና እንደሆነ ተገልጿል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት÷ ላለፉት 65 ዓመታት ኢትዮጵያ በርካታ የረጅም ርቀት ሯጮችን ለዓለም አበርክታለች።

ሩጫ በኢትዮጵያ ትልቅ ታሪክና ቦታ አለው ያሉት ከንቲባዋ÷ ሻምበል አበበ ቢቂላ በ1952 ዓ.ም በጣሊያን ሮም በተካሄደው የኦሊምፒክ ማራቶን በባዶ እግሩ ሮጦ ታሪካዊ ድል በማስመዝገብ ለሀገሩ የወርቅ ሜዳሊያ ማምጣቱን አስታውሰዋል።

በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ጀግና አትሌቶች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም መድረክ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላለፉት 25 ዓመታት የመዲናችን ብሎም የኢትዮጵያ መገለጫና ተናፋቂ የአደባባይ ስፖርታዊ ክንውን ነው ብለዋል።

በሁለቱ ዘርፎች ዕውቅና መሰጠቱ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪነት የሚያጎላ እንደሆነ ተናግረዋል።

ጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላን፣ የታላቁ ሩጫ ውድድር መስራች አትሌታችን ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴን እና ውድድሩን ባማረ ሁኔታ ሲያካሂዱ የቆዩትን ሁሉ አመስግነዋል።

በእውቅና መርሐ ግብሩ ላይ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፣ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ እንዲሁም በዓለም አትሌቲክስ የቅርስ ዳይሬክተር ክሪስ ተርነር ተገኝተዋል።

በጀማል አህመድ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
Facebook https://web.facebook.com/fanasport
Facebook WMCC
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

Exit mobile version