አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዘንድሮ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የቡና ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው አለ፡፡
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታጋይ ኑሩ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የቀይ ቡና ለቀማ ተጀምሯል።
አርሶ አደሩ ከለቀማ ጀምሮ እንዴት ማዘጋጀት እና ማጠራቀም እንዳለበት ግንዛቤ እንዲያገኝ የንቅናቄ ስራ መሰራቱን ገልጸው፤ የዋጋ ትመና ስራዎች በባለስልጣኑ አማካኝነት እየተሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ምርታማነትን ለማሳደግ ያረጁ ቡናዎችን የመጎንደል እና በአዲስ የቡና ተክሎች የመተካት ስራዎች ባለፉት ዓመታት ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከቡና ምርት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ የቡና ፓኬጅ ስትራቴጂ ተነድፎ ወደስራ መግባቱን ጠቅሰው÷ በዚህም ከፍተኛ የጥራት መሻሻል መታየት ጀምሯል ነው ያሉት።
ዘንድሮ ከፍተኛ ውጤት ከዘርፉ እንደሚጠበቅ ገልጸው፤ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የቡና ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
በመቅደስ የኔሁን

