Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በዞኑ ከ1 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል በላይ የዝንጅብል ምርት ይጠበቃል

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከምባታ ዞን ዘንድሮ ከ1 ሚሊየን 968 ሺህ ኩንታል በላይ የዝንጅብል ምርት ይጠበቃል፡፡

20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል በሚያስተናግደው ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምልከታ እያደረገ የሚገኘው የሚዲያ ባለሙያዎች ቡድን በከምባታ ዞን ሀደሮ ጡንጦ ወረዳ የዝንጅብል ልማትን ተመልክቷል።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ ተሾመ ሄራሞ በወቅቱ እንዳሉት÷ በዞኑ ሀደሮ ጡንጦ ዙሪያ እና ቃጫቢራ ወረዳዎች ዝንጅብል በስፋት ይመረታል።

ዘንድሮ በዞኑ በዝንጅብል ሰብል ከተሸፈነው 8 ሺህ 200 ሄክታር በላይ መሬት ከ1 ሚሊየን 968 ሺህ በላይ የዝንጅብል ምርት እንደሚጠበቅ ገልፀዋል፡፡

የሀደሮ ጡንጦ ወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤት ሃላፊ ሀብታሙ ዮሐንስ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በወረዳው 5 ሺህ 800 ሄክታር መሬት በዝንጅብል መሸፈኑን ገልጸዋል።

ከዚህም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል በላይ የዝንጅብል ምርት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በሀደሮ ከተማ የዝንጅብል የገበያ ማዕከል በመከፈቱ ምርቱ ወደ ሁሉም የኢትዮጵያ አቅጣጫዎች እንደሚጫን ተናግረዋል፡፡

ገበያው ላይ የሚስተዋለውን ህገ ወጥ የደላሎች ሰንሰለት ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በማርታ ጌታቸው

Exit mobile version