Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አዋሽ ባንክ ጠቅላላ የሃብት መጠኑ 442 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ደረሰ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዋሽ ባንክ ጠቅላላ ሃብት 442 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ደርሷል አሉ የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፀሐይ ሽፈራው።

የባንኩ የባለአክስዮኖች 30ኛ ዓመታዊ መደበኛ ጉባኤ እና 18ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ እየተካሄደ ነው።

በጉባኤው የአዋሽ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፀሐይ ሽፈራው እንዳሉት÷ ባንኩ በሂሳብ ዓመቱ 25 ነጥብ 67 ቢሊየን ብር ያልተጣራ ትርፍ አስመዝግቧል።

ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 137 በመቶ እድገት ማሳየቱንና ከፍተኛ ትርፍ መሆኑን አንስተዋል።

የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ 358 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር መሆኑን ገልጸው÷ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 125 ነጥብ 9 ቢሊየን እድገት ማሳየቱን ጠቁመዋል።

ባንኩ በሂሳብ ዓመቱ ከ2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት መቻሉንና የተሰጠ የብድር ክምችትም 20 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።

የባንኩ የተከፈለ ካፒታል 27 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ደርሷል ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው÷ ይህም ብሄራዊ ባንክ ነባር ባንኮች በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሊደርሱበት ይገባል ብሎ ካስቀመጠው የካፒታል መጠን የሚበልጥ መሆኑን አስረድተዋል።

ባንኩ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ረገድ 600 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓልም ነው ያሉት።

የአዋሽ ባንክ አጠቃላይ ባለአክስዮኖቹ 12 ሺህ 142 ሲሆኑ÷ ከ15 ሚሊየን በላይ ደንበኞች ማፍራቱም ተገልጿል።

በተጠናቀቀው የሂሳብ ዓመት 52 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት የቅርንጫፎቹን ቁጥር 989 አድርሷልም ነው የተባለው።

በጉባኤው ባንኩ ከደረሰበት ደረጃና አሁን ከመጡ ለውጦች ጋር እንዲጣጣም የሚያስችሉ የመመስረቻ ጽሑፍ ድንጋጌዎች የማሻሻያ ሃሳብ ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከባለአክሲዮኖች ጋር ውይይት ተደርጎ የውሳኔ ሃሳብ እንደሚቀርብም ተመላክቷል።

በእየሩሳሌም አበበ

Exit mobile version