Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አቶ አቤ ሳኖ የዓለም አቀፍ ኢስላሚክ ሪቴል ባንኪንግ የ2025 ምርጥ የባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽልማትን አሸነፉ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት እንዲስፋፋ በሰጡት ቁርጠኛ አመራር የዓለም አቀፍ ኢስላሚክ ሪቴል ባንኪንግ የ2025 ምርጥ የባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽልማትን አሸንፈዋል።

አቶ አቤ ሳኖ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ÷ አገልግሎቱ በኢትዮጵያ እንዲጀመር እና አሁን ለደረሰበት ከፍተኛ የእድገት ደረጃ ወሳኝ ሚና መጫወታቸውን አስረድተዋል፡፡

በተለይ አገልግሎቱን ለመጀመር የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎችን ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር በመቅረጽ በባንክ ደረጃ በቀዳሚነት ለመጀመር አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አንስተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ባካሄዷቸው ስትራቴጂያዊ ለውጦች ሲቢኢ ኑርን በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ መሪ ማድረጋቸውን ነው ያብራሩት፡፡

ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት እንዲስፋፋ በማድረግ በፋይናንስ አካታችነት ያበረከቱት አስተዋፅኦ ለዓለም አቀፍ ኢስላሚክ ሪቴል ባንኪንግ የ2025 ምርጥ የባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሽልማት አብቅቷቸዋል።

በ11ኛው ዓለም አቀፍ ኢስላሚክ ሪቴል ባንኪንግ ሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሲቢኢ ኑር አገልግሎት በምስራቅ አፍሪካ ምርጥ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ሽልማትን ተቀዳጅቷል፡፡

ኢትዮጵያ በዘርፉ በዓለም ከ80 ሀገራት ሞሮኮን፣ ናይጄሪያን እና ኬንያን በመብለጥ 27ኛ ደረጃን መያዝ መቻሏን የባንኩ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አልሰን አሰፋ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡

Exit mobile version