Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአካታችነት ኢትዮጵያዊ ማንነትን መገንባት ያስፈልጋል – ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአካታችነት፣ በአቃፊነትና በአሳታፊነት አውድ ኢትዮጵያዊ ማንነትን መገንባት ያስፈልጋል አሉ የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፡፡

ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ የምንሰራት ኢትዮጵያ ከሁሉም ለሁሉም በሁሉም የሆነች መሆን አለባት ብለዋል፡፡

ሰዎች የተለያየ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ብሔር እና ባህል እንዳላቸው አንስተው፥ ነገር ግን እነዚህ ልዩነቶች የጋራ ማንነትን የሚገድቡ አለመሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ሰዎች ብዝሃነትን ማካተትና ማቀፍ ሲያቅታቸው ማዶ ለማዶ እንደሚቆሙ የገለጹት ኃላፊው፥ ብዝሃነት ውበትና ጌጥ እንጂ የልዩነት ምንጭ ሊሆን እንደማይችል አስረድተዋል፡፡

አንዳንድ ኃይሎች የፖለቲካ ሃሳባቸውን አንጸባርቀው፣ አሳምነውና ኃይል አሰባስበው ሀገር ለመገንባት የሚያስችል አጀንዳ ማምጣት ሲሳናቸው ስልጣን ለመቆናጠጥ ማንነትን እንደ መሰላል ይጠቀማሉ ብለዋል፡፡

የሰዎች ማንነት መከበርና በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ መካተት እንዳለበት ጠቁመው፥ የምንገነባው ግን ታላቋን ኢትዮጵያ መሆን አለበት ነው ያሉት፡፡

ትልቅ ማንነት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ዋናው ማጠንጠኛ ሀገራዊ ማንነት መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

በዚህ ሂደት ብሔርን፣ ቋንቋን እና ሃይማኖትን በመምዘዝ ስልጣን ለመቆናጠጥ እንደ መሰላል መጠቀም የሚፈልጉ አካላት አጀንዳ እንደሚያጡ ገልጸዋል።

በብርሃኑ አበራ

Exit mobile version