አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በቀጣናው ብሎም በአፍሪካ ያላት ተደማጭነት እና ተፅዕኖ በቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ ላይ እንድትሳተፍ አስችሏታል አሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተሳተፈ ሲሆን፥ ከጉባኤው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት መሪዎችና ከተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውጤታማ የሁለትዮሽ ውይይቶችን አድርጓል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ልዑኩ በጉባኤው ላይ የነበረውን ቆይታ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፥ ኢትዮጵያ በጉባኤው ላይ እንድትሳተፍ የተጋበዘችው በአህጉሪቱ ባላት ተደማጭነትና ተጽዕኖ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ያለው ፈጣን ኢኮኖሚ፣ በመንግስት እየተከናወኑ ያሉ የለውጥ ስራዎችና በቀጣናው እንዲሁም በአፍሪካ ያላት ተፅዕኖ በጉባኤው እንድትሳተፍ አስችሏታል ነው ያሉት፡፡
በአፍሪካ አህጉር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው የቡድን 20 ስብሰባ ላይ መሳተፍ መቻሏ ለኢትዮጵያ ትልቅ ፖለቲካዊ ትርጉም እንዳለው አስረድተዋል፡፡
የመሪዎች ጉባኤው የአፍሪካውያን ደምፅ የሚሰማበት መድረክ እንዲሆን ጥረቶች ተደርገዋል ያሉት ሚኒስትሯ÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ ይህን የሚያጠናክር ንግግር ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን ዘርፈ ብዙ የለውጥ ስራዎች በተመለከተ ገለጻ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡
የዓለም አስተዳደር ችግሮችን፣ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ተግዳሮቶችን እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ የኢትዮጵያን አቋም አንጸባርቀዋል ነው ያሉት፡፡
ሚኒስትሯ በማብራሪያቸው ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያከናወነቻቸው ባሉ የለውጥ ስራዎች ምክንያት ተሰሚነቷ እየጎላ መምጣቱን ጠቅሰው፥ በጉባኤው መሳተፏም ይህን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ

