አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መድን ድርጅት 50ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን እያከበረ ይገኛል፡፡
ከተመሰረተ 50 ዓመታትን ያስቆጠረው ድርጅቱ ለቀጣይ ሁለት ወራት የሚያከናውነውን የወርቅ እዮቤልዩ ክብረ በዓሉን በይፋ አስጀምሯል።
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቤል ታደሰ በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ እንዳሉት፥ ተቋሙ በመድን ኢንዱስትሪ ፈር ቀዳጅ በመሆን ስኬታማ ስራ አከናውኗል።
ድርጅቱ ሲመሰረት የነበረው የዋስትና መጠን 9 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር የነበረ ሲሆን አሁን ላይ 12 ነጥብ 8 ትሪሊየን ብር ደርሷል ነው ያሉት።
ድርጅቱ ሲመሠረት ጠቅላላ የተከፈለ ጉዳት ካሣ 17 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር እንደነበር አስታውሰው፥ አሁን ላይ 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር መድረሱን ገልጸዋል፡፡
የድርጅቱ ጠቅላላ ሀብት 24 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር መድረሱንና ያሉትን ቅርንጫፎች ከ130 በላይ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በሐመልማል ዋለ

