Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለኢትዮጵያ የአህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ ውጤታማነት በቅንጅት መስራት ይገባል – የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ ውጤታማ በማድረግ በአህጉሪቱ ገበያ ያላትን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ በቅንጅት መስራት አስፈላጊ ነው አሉ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ፡፡

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ና የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም አነስተኛና መካከለኛ የንግድ ተቋማት ለኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ ውጤታማነት ያላቸውን ሚና በተመለከተ ያዘጋጁት የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ቁርጠኝነት ስምምነቱን ማጽደቋ ወሳኝ ርምጃ ነው፡፡

ነገር ግን ስምምነቱን ማጽደቋ ብቻውን ተቋማዊ ጥንካሬ፣ የቁጥጥር ግልጽነትና ለሙሉ ትግበራ የሚያስፈልገውን የሎጂስቲክስ ብቃት መፍጠር እንደማያስችል አመልክተዋል።

የኢትዮዽያን አህጉራዊ የንግድ ተወዳዳሪት ከፍ ለማድረግ በአንድ ተቋም ብቻ ለውጥ ስለማይመጣ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ በአህጉሪቱና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንድትሆን የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ የጋራ ጥረት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፥ የተጠናከረ ተቋማዊ አቅም፣ የባለ ድርሻ አካላት ቅንጅት፣ የተሻሻለ የጉምሩክ ስርዓት መፍጠር ይገባል ነው ያሉት።

አፍሪካ የአህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን የወደፊት ኢኮኖሚዋ ማዕከል አድርጋዋለች ያሉት ዳይሬክተሩ፥ ይህም ምርትን ለማስፋፋት፣ የወጪ ንግድን ለማሳደግና ተወዳዳሪ የእሴት ሰንሰለቶችን ለመገንባት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

Exit mobile version