Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና በሱዳን ድንበር አካባቢ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪን ተቀበሉ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና በሱዳን አጎራባች አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂ ሃይሎች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ክልሉ ገብተዋል፡፡

ታጣቂ ሃይሎቹ ትጥቃቸውን ፈተው ወደ ክልሉ ከገቡ በኋላ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን ጋር ተወያይተዋል፡፡

አቶ አሻድሊ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የክልሉን ሁለንተናዊ ሰላም ለማረጋገጥ እየተከናወነ የሚገኘው ሥራ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ሃይሎችም የሰላም ጥሪን በመቀበል በሰላማዊ መንገድ ሃሳባቸውን ማራመድ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ትጥቃቸውን የፈቱት ታጣቂ ኃይሎች በሱዳን አጎራባች እና ጉባ ወረዳ የተለያዩ ሥፍራዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ሻዕባን አባስ እና ባድቆ ሳኚ በተሰኙ ግለሰቦች ይመሩ የነበሩት ታጣቂዎች ወደ ሠላማዊ መንገድ መመለስ ለበርካቶች አርአያ እንደሚሆን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የሰላም ጥሪን የተቀበሉት ታጣቂ ሃይሎች ወደ ተሃድሶ ሥልጠና ማዕከል መግባታቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ መለሰ በየነ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡

ከተሃድሶ ስልጠና በኋላም በክልሉ የተለያዩ ዘርፎች ላይ በመሰማራት የልማት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስገንዝበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version