አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በከፊል ከሰለጠኑ ሠራተኞች በተጨማሪ በዲግሪና ከዛ በላይ ለሰለጠኑ ሠራተኞች ሰፊ የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት እየተሰጠ ነው አለ የሥራና ክህሎት ማኒስቴር፡፡
በማኒስቴሩ የኢትዮጵያ ሥራ ገበያ ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አለቃ ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ ÷ ከዚህ በፊት 4 የነበሩት የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት መዳረሻዎች አሁን ላይ ወደ 8 ከፍ ማለታቸውን አውስተዋል፡፡
ከዚህ በፊት የነበሩት የቤት ውስጥ ሥራ ላይ ብቻ ያተኮሩ ስምምነቶች የሰለጠነ የሰው ኃይል ወደ መላክ መሸጋገራቸውንም ተናግረዋል።
ማንኛውም ወደ ውጭ ሀገር ተጉዞ ሥራ ማግኘት የሚፈልግ ሰው በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ፈላጊ መረጃ ቋት ውስጥ በመመዝገብ ከዚህ በፊት ከነበረው በከፊል ከሰለጠነው እስከ ዲግሪና ከዚያም በላይ በሰለጠነበት የሙያ መስክ ሥራ ማግኘት እንደሚችል አብራርተዋል፡፡
ምዝገባው በቀጥታ በኦንላይን የሚከናወን በመሆኑ ሥራ ፈላጊዎች በቀበሌያቸው አሊያም በየወረዳው ለዚሁ ተብለው በተዘጋጁ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች መመዝገብ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
ዜጎች በተለያዩ ሀገራት በሕገ ወጥ መንገድ ሥራ እናስቀጥራችኋለን የሚሉ ደላሎችንና ተቋማትን ለሚመለከተው አካል ጥቆማ በመስጠት እንዲያጋልጡ ጠይቀዋል፡፡
ለሲኦሲ ብቃት ምዘናም ሆነ ወደ ውጭ ሀገር ለመሄድ የሚከፈል ምንም ዓይነት ገንዘብ እንደሌለም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በሄኖክ በቀለ

